ኮርፖሬሽኑ መሬት ወስደው ባላለሙ 43 ባለሃብቶች ላይ አስተዳደራዊ እርምጃ መውሰዱን አስታወቀ

3

ደሴ ግንቦት 25/2014 /ኢዜአ/ በአማራ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን የኮምቦልቻ ቅርንጫፍ በኢንቨስትመንት ስም መሬት ወስደው በገቡት ውል መሰረት ባላለሙ 43 ባለሃብቶች ላይ በሕግ አግባብ አስተዳደራዊ እርምጃ መውሰዱን አስታወቀ፡፡

የቅርንጫፉ ኃላፊ አቶ እሸቱ አሊ በሰጡት መግለጫ እንዳሉት አምራች ባለሃብቶችን በማበረታታት ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን በሀገር ውስጥ ለመተካት መንግስት ልዩ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ ነው።

በባለሃብቶች የሚነሱ የመሰረተ ልማትና የመልካም አስተዳደር ችግሮችንም በየደረጃው በቁርጠኝነት እየፈታ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡

ድጋፍ ተደርጎላቸውና ምቹ ሁኔታ ተፈጥሮላቸው ማልማት ያልቻሉትን ደግሞ መሬታውን ነጥቆ ለሚያለሙ ባለሃብቶች መስጠት የግድ የሆነበት ወቅት ላይ እንገኛለን ብለዋል።

በመሆኑም በቅርንጫፉ ድጋፍ ተደርጎላቸው በውላቸው መሰረት የተረከቡትን መሬት ባላለሙ 43 ባለሃብቶች ላይ ኮርፖሬሽኑ ሕጋዊ እርምጃ እንዲወስድ መገደዱን ተናግረዋል።

በዚህም ከዘጠኝ ባለሃብቶች 6 ነጥብ 8 ሄክታር መሬት የነጠቀ ሲሆን፤ ለ29 ባለሃብቶች የመጨረሻ ማስጠንቀቂያና ለአምስቱ ደግሞ የመጀመሪያ ማስጠንቀቂያ መስጠቱን አስረድተዋል።

ባለሃብቶቹ ከ2005 ዓ.ም ጀምሮ በኢንቨስትመንት ስም መሬት ወስደው በውላቸው መሰረት ያላለሙ፣ አጥረው ያስቀመጡና የወሰዱትን መሬት ለሌላ ዓላማ ያዋሉ ናቸው ብለዋል።

በገቡት ውል መሰረት የወሰዱትን መሬት ካላለሙ ባለሃብቶች በሕግ አግባብ የተወሰደውን መሬት ማልማት ለሚችሉ ባለሃብቶች እንደሚሰጥ አስታውቀዋል።

ቀደም ሲል በባለሃብቶቹ ይነሱ የነበሩ የመሰረተ ልማትና የመልካም አስተዳደር ችግሮች ተፈተው እንደነበር ጠቁመዋል።

እንደ ኃለፊው ገለጻ ከባለፈው ዓመት ጀምሮ በቅንጅት በተከናወነ ስራ በ25 ነጥብ 3 ሚሊዮን ብር የውሃ፣ የመንገድና የኤሌክትሪክ መብራት ችግሮችን መፍታት ተችሏል።

እንዲሁም የኤሌክትሪክ ኃይል እጥረትን በማቃለል የአምራች ኢንዱስትሪዎችን የማምረት አቅም ለማሳደግ በዚህ ዓመት 31 ሚሊዮን ብር ተመድቦ ከከሚሴ-ሀርቡ ከፍተኛ መስመር ዝርጋት እየተካሄደ ነው ብለዋል።

በአማራ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ኮምቦልቻ ቅርንጫፍ 155 ባለሃብቶች 365 ሄክታር መሬት ወስደው ወደስራ መግባታቸውም ተገልጿል።

ባለሃብቶቹ በግብርና ውጤቶች ማቀነባበሪያ፣ በአምራች ኢንዱስትሪና በኮንስትራክሽን ዘርፎች የተሰማሩ ሲሆን፤ ከ2 ሺህ ለሚበልጡ ዜጎች የስራ እድል መፍጠራቸውንም ለማወቅ ተችሏል።