“ህወሃት ሰብዓዊ ድጋፎችን ለጦርነት የማዋል ልምድ ያለው ድርጅት ነው፤ በአሁኑ ወቅትም ተመሳሳይ ድርጊት እየፈጸመ ይገኛል”

72

ግንቦት 24 ቀን 2014 (ኢዜአ) “ህወሃት ሰብዓዊ ድጋፎችን ለጦርነት የማዋል ልምድ ያለው ድርጅት ነው፤ በአሁኑ ወቅትም ተመሳሳይ ድርጊት እየፈጸመ ይገኛል” ሲል ዓለም አቀፉ ጋዜጠኛ አልስቴር ቶምሰን ተናገረ ፡፡


ከዚህ አኳያ ወደ ትግራይ ክልል እየገባ የሚገኘው እርዳታ ለህብረተሰቡ እየደረሰ አለመሆኑን የሚያነሱ ጋዜጠኞችና ታዛቢዎች ሃሳብ ተገቢ መሆኑንም ገልጿል፡፡


አሸባሪው ህወሃት ከምስረታው ጀምሮ በዜጎች ደምና ስቃይ በመነገድ የሚታወቅ ድርጅት ሲሆን፤ በ1977 ዓ.ም በትግራይ በተከሰተው ረሃብ የፈጸመው ዘግናኝ ድርጊት ደግሞ ለዚህ ጥሩ ማሳያ ነው፡፡


ቡድኑ ከደርግ መንግስት ጋር የትጥቅ ትግል እያደረገ በነበረበት በ1977 ዓ.ም በትግራይ እጅግ አስከፊ ረሃብ መከሰቱ ይታወሳል፡፡


ወትሮውንም ለህዝብ ደንታ የሌለው ይህ ቡድን በረሃብ የሚረግፉ ዜጎችን ሰቆቃ እንደ መልካም አጋጣሚ በመጠቀም ከመላው ዓለም የተራድኦ ድርጅቶች፣ ግለሰቦችና ተቋማት የሚቀርበውን እርዳታ ለመሳሪያ ግዥ ተጠቀመበት፡፡


በአንድ ወቅት የእንግሊዙ ታወቂ የቴሌቭዥን ጣቢያ (ቢቢሲ) ባሰራጨው መርማሪ ዘገባ ህወሃት በወቅቱ በእርዳታ ከሚቀርበው እህል ውስጥ 5 በመቶውን ብቻ ለህብረተሰቡ በማድረስ ቀሪውን ለመሳሪያ ግዥ ይጠቀምበት እንደነበር ከቡድኑ መስራቾች መካከል ዶክተር አረጋዊ በርሄን ጠቅሶ መዘገቡ አይዘነጋም፡፡


በዚህም በትግራይ በርካታ ዜጎች በረሃብና ቸነፈር ምክንያት ለሞት ተዳርገዋል፡፡


“ድመት መንኩሳ አመሏን አትረሳ” እንዲሉ አሸባሪው ህወሃት አሁንም ወደ ትግራይ የሚገባውን እርዳታ ለጦርነት ዓላማ እየተጠቀመበት መሆኑን የሚያነሱ ዓለም አቀፍ ጋዜጠኞችና ታዛቢዎች ተበራክተዋል፡፡


ኒውዝላንዳዊው ጋዜጠኛ አልስቴር ቶምሰን ከኢዜአ ጋር በነበረው ቆይታ አሸባሪው ህወሃት ሰብዓዊ ድጋፎችን ለጦርነት የማዋል ልምድ ያለው ድርጅት መሆኑን አንስቷል፡፡


የሽብር ቡድኑ በ19 80ዎቹ በሰሜን ኢትዮጵያ ተከስቶ የነበረውን ረሃብ ተከትሎ ከዓለም አቀፍ ተራድኦ ድርጅቶች ይቀርብ የነበረውን ሰብዓዊ ድጋፍ ለጦር መሳሪያ ግዥ እንዳዋለው አስታውሷል።


ቡድኑ አሁንም ተመሳሳይ ድርጊት እንደሚፈጽም ነው ጋዜጠኛው የሚያብራራው፡፡
የሽብር ቡድኑ እርዳታ ጭነው ወደ ትግራይ ክልል የገቡ ተሽከርካሪዎችን በማገት ለጦርነትና በወረራ ይዟቸው በነበሩ አካባቢዎች ንብረት ለመዝረፍ መጠቀሙንም ነው የገለጸው፡፡


ቡድኑ የእርዳታ መጋዝኖችን በመዝረፍ ጭምር የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ሃብትን ለጦርነት ማዋሉ ግልጽ ነው ሲል አብራርቷል፡፡


“የመንግስታቱ ድርጅት ይህን የቡድኑን ህገ-ወጥ አካሄድ በግልጽ ሲያወግዝ አይታይም፤ ይህም ተቀባይነት የሌለውና የዓለም አቀፍ መርሆችን የጣሰ አካሄድ ነው” ብሏል፡፡


ከዚህ አኳያ ዓለም አቀፍ የእርዳታ ድርጅቶች ጉዳዩን በሚመለከት ጥያቄ ላላቸው አካላት ምላሽ ሊሰጡ እንደሚገባም ነው የተናገረው፡፡


ቡድኑ በተለይ በአፋር ክልል የእርዳታ መስመሮች ላይ ወረራ በመፈጸም ሰብዓዊ ድጋፍ ወደ ትግራይ እንዳይገባ ሲፈጽም የነበረውን ህገ-ወጥ ተግባር የዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ሊገነዘብ እንደሚገባም ተናግሯል፡፡


በመሆኑም የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ወደ ትግራይ ክልል የሚላከውን ሰብዓዊ እርዳታ ለምን ዓላማ እየዋለ መሆኑን በአግባቡ ማጣራት እንደሚጠበቅበት ተናግሯል፡፡


በተያያዘ የዓለም የጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ቴድሮስ አድሃኖም ከድርጅቱ መርህ ባፈነገጠ መልኩ በሰሜን ኢትዮጵያ ስላለው ሁኔታ የተሳሳተ መረጃ እያሰራጩ መሆኑን ጋዜጠኛው ተናግሯል፡፡


በመሆኑም የመንግስታቱ ድርጅት የዓለም የጤና ድርጅትን ጨምሮ በስሩ ያሉ ተቋማትን አሰራር መለስ ብሎ ሊመረምር ይገባል ነው ያለው፡፡


የዓለም የጤና ድርጅትን ዋና ዳይሬክተር እያከናወነ ያለው ተግባር ትክክል አለመሆኑ በግልጽ ሊነገረው እንደሚገባም ነው ያነሳው፡፡


ኢትዮጵያን እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ