የእምቦጭ አረም ከ5 ሺህ ሄክታር በላይ በሚሆነው በአባያና ጫሞ ሐይቆች ላይ በፍጥነት እየተስፋፋ ነው

254

አርባ ምንጭ፤ ግንቦት 24/ 2014 (ኢዜአ) የእምቦጭ አረም ከ5 ሺህ ሄክታር በላይ በሚሆነው በአባያና ጫሞ ሐይቆች ላይ በፍጥነት እየተስፋፋ መሆኑን የደቡብ ክልል ደን፣ አካባቢ ጥበቃና ልማት ቢሮ ትብብር ጠየቀ፡፡

የቢሮው ምክትል ኃላፊ አቶ ሳሙኤል ቀቀቦ ለኢዜአ እንዳስታወቁት በሐይቆቹ ላይ ጉዳት እያደረሰ ያለውን የእምቦጭ አረም ለማስወገድና ስርጭቱን ለመግታት ሐይቆቹ የሚነኳቸው ክልሎችና የሚመለከታቸው አካላት ትብብር ያስፈልጋል።

የእምቦጭ አረሙ መስፋፋት በውሃው ውስጥና ከውሃው ውጭ የሚገኙ ብዝሃ ሀብቶች ላይ እንዲሁም ኑሮአቸውን በሐይቆቹ ላይ ባደረጉ የዓሣ አስጋሪ ማህበራት ላይ ስጋት መደቀኑን ገልጸዋል፡፡

ባለፉት ሶስት ዓመታት በህዝብ ንቅናቄ የእምቦጭ አረምን ለማስወገድ  ጥረት መደረጉን ጠቁመው፤ የሚፈለገውን ውጤት ለማምጣት የባለድርሻ አካላት ሚና ማስፈለጉን  ተናግረዋል፡፡

በተለይ የአባያ ሐይቅን የሚዋሰኑት የደቡብ፣ ሲዳማና የኦሮሚያ ክልሎች ትብብር እንዲያደርጉ ጠይቀዋል።

ችግሩን ለመፍታት ከስምጥ ሸለቆ ተፋሰስ ባለስልጣን ጋር እየመከሩ መሆናቸውን አቶ ሳሙኤል አስታውቀዋል፡፡

የጋሞ ዞን ደን፣ አካባቢ ጥበቃና ልማት መምሪያ ኃላፊ አቶ ማዜ ሸቀነ በበኩላቸው  በአባያና ጫሞ ሐይቆች ላይ የተከሰተውን የእምቦጭ አረም ለማስወገድ ባለፉት ሶስት ዓመታት የህዝብ ንቅናቄ መደረጉን አመልክተው፤ በዚህም በ1ሺህ 240 ሄክታር ላይ የነበረ  የእምቦጭ አረም መወገዱን ገልጸዋል፡፡

ከሁለት ዓመታት በፊት ከ2 ሺህ ሄክታር በታች የነበረው የእምቦጭ አረም በአሁኑ ሰዓት በአርባ ምንጭ ከተማ፣በአርባ ምንጭ ዙሪያና በምዕራብ አባያ ወረዳዎች በሚገኙ 17 ቀበሌዎች መስፋፋቱን አስረድተዋል፡፡

ሐይቆቹ የሀገሪቱ ብሎም የምስራቅ አፍሪካ ሀብት እንደመሆናቸው የእምቦጭ አረሙን በሳይንሳዊ መንገድ ለማስወገድ የባለድርሻ አካላት ቅንጅት እንደሚያስፈልግ አመልክተዋል፡፡

''የስርዓተ ምህዳር ካንሰር የሆነው የእንቦጭ አረም በውሃማ አካል ላይ የእንስሳትና እጽዋት ብዝሀ ሀብት የሚያጠፋ አረም ነው'' ያሉት ደግሞ  በጋሞ ዞን አካባቢ ጥበቃና ደን ልማት ጽህፈት ቤት የብዝሀ ህይወት ልማትና ጥበቃ ባለሙያ አቶ ጋንቡራ ጋንታ ናቸው፡፡

የእንቦጭ አረም ውሃን በማትነን በውሃ መጠን ላይ ከፍተኛ ጉዳት ከማስከተልም በላይ የኦክሲጅን እጥረት በመፍጠር ዓሣን ጨምሮ በውሃ ውስጥ የሚገኙ እንስሳት ዝርያን ሊያጠፋ እንደሚችልም አብራርተዋል፡፡

በሐይቆቹ ከተስፋፋው የእምቦጭ አረም በአብዛኛው የሚገኘው በጋሞ ዞን መሆኑን የተናገሩት አቶ ጋንቡራ፤ የሀይቆቹ መጋቢ ወንዞች ከተራራማ ስፍራዎች ይዘውት የሚመጡት ደለል አፈር  ዋነኛው ምክንያት መሆኑን ጠቁመዋል።

የእምቦጭ አረም በጣና ሐይቅና በሌሎች የሀገሪቱ ውሃማ አካላት ላይ እያደረሰ ያለውን ጉዳት ለመቀነስ ሕዝብ የተሳተፈባቸው ዘመቻዎች መካሄዳቸው ይታወሳል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም