በክልሉ የመጀመሪያው የባህል ፌስቲቫልና ኤግዚቢሽን ነገ በቦንጋ ከተማ ይከፈታል

101

ሚዛን አማን፣ ግንቦት 24/2014 (ኢዜአ) በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል የመጀመሪያው የባህል ፌስቲቫልና ኤግዚቢሽን ነገ በቦንጋ ከተማ መካሄድ እንደሚጀምር የክልሉ ባህል ቱሪዝምና ስፖርት ቢሮ አስታወቀ።

"ባህላችን ለዘላቂ ሠላምና ለአንድነታችን" በሚል መሪ ሀሳብ የሚካሄደው ፌስቲቫል ከነገ ጀምሮ ለሶስት ቀናት በቦንጋ ከተማ ብሔራዊ የቡና ሙዚየም እንደሚካሄድ ተገልጿል።

በቢሮው የባህል ቱሪዝም ዘርፍ ምክትል ኃላፊ አቶ አክሊሉ ለማ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ የሚካሄደው የባህል ፌስቲቫልና ኤግዚቢሽን ክልሉ ከተደራጀ ጀምሮ ለመጀመሪያ ጊዜ መሆኑን ተናግረዋል።

ፊስቲቫሉ በክልሉ የሚገኙ ብሔር ብሔረሰቦች ያላቸውን ቱባ ባህል የሚያስተዋውቁበት መድረክ መሆኑን ተናግረዋል።

የክልሉ ህዝቦች በማኅበራዊ እንቅስቃሴያቸው የሚገለገሉባቸው ባህላዊ ቁሳቁሶችን ጨምሮ ባህላዊ ክዋኔዎች፣ አልባሳትና ባህላዊ ምግቦችና መጠጦች በፌስቲቫሉ እንደሚቀርቡ ጠቅሰዋል።

በፌስቲቫሉ የፎቶ አውደርእይና የፓናል ውይይት እንደሚካሄድም ጠቁመዋል።

በባህል ፌስቲቫልና ኤግዝቢሽን ላይ ለሚታደሙ እንግዶች ሀገራዊ አንድነትን በሚያንጸባርቁ ዝግጅቶች ለማስተናገድ ዝግጅት መደረጉን ገልጸዋል።

በዝግጅቱ ላይ በክልሉ የሚገኙ የዞን አመራሮች፣ የሀገር ሽማግሌዎችና የሃይማኖት አባቶች እንደሚገኙ አቶ አክሊሉ አብራርተዋል።

በፊስቲቫሉ ላይ ከተለያዩ ክልሎች የመንግስት የስራ ሃላፊዎች እንሚታደሙም ጠቁመዋል ።

በሰኔ 08/2014 ዓ/ም በሀገር አቀፍ ደረጃ በሚካሄደው የባህል ፌስቲቫል ላይ ክልሉን በመወከል የሚሳተፉ የባህል ልዑካን እንደሚመረጡም ተመላክቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም