ድሬዳዋን በምግብ ዋስትና ራሷን ለማስቻል እየተሰራ ነው

212

ድሬዳዋ፤ ግንቦት 24/2014 (ኢዜአ) የከተማ ግብርናን በተቀናጀ መንገድ በማካሄድ ድሬዳዋን በምግብ ዋስትና ራሷን የቻለች ከተማ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን የድሬዳዋ አስተዳደር ግብርና ውሃና ማዕድን ኢነርጂ ቢሮ አስታወቀ።

የድሬዳዋ አስተዳደር ግብርና፣ ውሃ፣ ማዕድንና ኢነርጂ ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ኤሊያስ አልይ ለኢዜአ እንዳሉት፤ በድሬዳዋ የከተማ ግብርና ሥራ ከመቶ ዓመት የዘለለ ልምድ እንዳለው ማረጋገጫው በመኖሪያ ቤትና በተቋማት ውስጥ የሚመረቱ የፍራፍሬ ምርቶች ናቸው።

ይህን ዘመን የተሻገረ ልምድ ከቅርቡ ዓመታት ወዲህ ደግሞ በፍራፍሬ፣ በአትክልት፣ በእንስሳት እርባታ፣ በዶሮና እንቁላል ምርት ማጠናከር ተችሏል።

በግልና በማህበራት በ280 ማሳዎች ላይ እየተካሄደ ያለው የከተማ ግብርና ስራም ውጤት እየተመዘገበበት መሆኑን ተናግረዋል።

በተለይ እንደ ሀገር ተጠናክሮ የተጀመረው የከተማ ግብርናን ተከትሎ በድሬዳዋም ለዘርፉ ልዩ ትኩረት ተሰጥቶት እየተሰራ  ነው ብለዋል።

አቶ ኤሊያስ እንዳሉት በአረጋዊያን መጦሪያ ማዕከላት፣ በግለሰብ ሰፋፊ ቦታዎች እና በመንግስት ተቋማት ውስጥ የተለያዩ አትክልቶችን በስፋት የማምረት እንቅስቃሴ እየተካሄደ ነው።

በዘርፉ ምርታማነትን ለማጎልበት ቢሮው ከሐረማያና ከድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲዎች የምርምር ማዕከላት ጋር በመቀናጀት ምርጥና የተዳቀሉ ዘሮችን በማቅረብ፣ ሙያዊ ድጋፍ በመስጠት፣ ክትትልና ቁጥጥር በማድረግ እየደገፈ መሆኑን ተናግረዋል።

አስተዳደሩ ለዘርፉ የሰጠው ትኩረት፣ድሬዳዋ ለከተማ ግብርና ያላት ምቹነት፣ እየተሰጡ የሚገኙ ድጋፎች ድሬዳዋን በአጭር ጊዜ ውስጥ በምግብ ዋስትና ራሷን የቻለች ከተማ ለማድረግ እየተሰራ ላለው ስራ ማረጋገጫ ነው  ብለዋል።

በድሬዳዋ የብልጽግና ጽህፈት ቤት ምክትል ኃላፊ አቶ ሻኪር አህመድ በበኩላቸው፣ በፅፈት ቤቱ ባለ ሰፊ ቦታ ላይ ሽንኩርት፣ ቃሪያ እና ቲማቲም ተተክለው በጥሩ ይዞታ ላይ መሆናቸውን ገልጸዋል።

ለተክሎቹ አስፈላጊው እንክብካቤ እየተደረገ መሆኑን ጠቁመው፣ "ምርቱ በአጭር ጊዜ ውስጥ ሲደርስ ሠራተኞች ተጠቃሚ ይሆናሉ" ብለዋል።

እንደ ኃላፊው ገለጻ ክፍት ቦታ ያላቸው ሁሉም ተቋማት በተመሳሳይ የከተማ ግብርና ልማት እንዲያካሂዱ ከግብርና ቢሮ ጋር በቅንጅት እየተሰራ ነው።

የግብርና ቢሮ ባደረገላቸው የተለያየ ሙያዊ እገዛ ተጠቅመው ከቤተሰብ ባገኙት 21 ሄክታር መሬት ላይ በማህበር ተደራጅተው በከተማ ግብርና አትክልትና ፍራፍሬ እያለሙ መሆኑን የገለጹት ደግሞ ወይዘሮ መሊካ አህመድ ናቸው።

የውሃ ጉድጓድ በማስቆፈር ወደ ልማት መግባታቸውን ገልጸው፣ "በአጭር ጊዜ ውስጭ ድሬዳዋን ብቻ ሳይሆን ሀገር የሚመግብ ጣፋጭ ብርቱካን እናመርታለን" ብለዋል።

ማህበሩ 18 አባላት እንዳሉት ጠቁመው፣ በአስተዳደሩ ግብርና ቢሮ እየተደረገላቸው ባለው ድጋፍ ውጤታማ እንደሚሆኑ ተናግረዋል።

ወይዘሮ መሊካ እንዳሉት አምና ካመረቱት የመንደሪን፣ ሀባብና ብርቱካን ምርት 1 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር ገቢ አግኝተዋል።

"ለም መሬት፣ ውሃና ልምድ ያለው ባለሙያ እያለን ከውጭ ፍራፍሬ አናስገባም፤ ድሬዳዋ በአትክልትና ፍራፍሬ የምትታወቅበትን ዝና ይበልጥ እናሳድጋለን" ብለዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ ለከተማ ግብርና ትኩረት መስጠታቸው በድሬዳዋ የምግብ ዋስትና ለማረጋገጥ መነቃቃት እንደፈጠረም ወይዘሮ መሊካ ተናግረዋል።

በድሬደዋ ሳብያን ቀበሌ ፓፓዬ፣ ሙዝና አትክልት ልማት ላይ የተሰማሩት ወይዘሮ አሚና አሊ በበኩላቸው፣ "የግብርና ቢሮ የሚያደርገው ድጋፍ በከተማው ጫፍ ለሚገኙ ነዋሪዎችም መሆን ይኖርበታል" ብለዋል።

የከተማ ግብርና ልማት በምግብ ዋስትና ራስን ከመቻል ባለፈ ምርትን ለገበያ ለማቅረብ ስለሚያግዝ ድጋፉ መጠናከር እንዳለበት ተናግረዋል።

በ1895 ዓ.ም ታህሳስ ወር ከጅቡቲ ድሬዳዋ የገባው ባቡር ለድሬዳዋ ከተማነት መሠረት መጣሉን መረጃዎች ያሳያሉ።

ከዚህ ጊዜ ጀምሮም  ነዋሪዎቿ በየመኖሪያ ቤታቸው በድሬዳዋ ብቻ የሚገኘውን አንበሾክን ጨምሮ ወይን፣ ሮማን፣ ዘይቱና፣ ሎሚ፣ ብርቱካን፣ መንደሪን፣ ሆምጣጤና ጊሽጣ በመኖሪያ ግቢያቸው በመትከል በፍራፍሬ ምርት ራሳቸውን ሲመግቡ መቆየታቸውን መረጃዎች ያሳያሉ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም