በከተማዋ የንባብ ባህልን ለማዳበር የወጣቶች የሰብዕና ማዕከላትን የማጠናከር ስራ በትኩረት እየተሰራ ነው- የአዲስ አበባ ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ

101

ግንቦት 24/2014/ኢዜአ/ የአዲስ አበባ ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ በከተማዋ የንባብ ባህልን ለማዳበር የወጣቶች የሰብዕና ማዕከላትን የማጠናከር ስራ እያከናወነ መሆኑን ገለጸ።

ቢሮው በሁለት ዙር ያሰባሰባቸውን ከ3ሺ በላይ መጻሕፍት ለአብርሆት ቤተ መጻሕፍት ዛሬ አስረክቧል።


በዚህ ወቅት ከኢዜአ ጋር ቆይታ ያደረጉት የአዲስ አበባ ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ ሃላፊ አቶ አብርሃም ታደሠ መጻህፍቱ  ወጣቶችንና የስፖርት ቤተሰቡን እንዲሁም የቢሮውን ሰራተኞች በማስተባበር በሁለት ዙር የተሰባሰቡ ናቸው ብለዋል።

መጻሕፍቱ ለወጣቶች ሰብእና ግንባታና ለትምህርት አጋዥ መሆናቸውን ጠቅሰው የወጣቶችን የንባብ ባህል ለማሳደግ በወጣቶች የሰብዕና ማዕከላት ውስጥ የሚገኙ ቤተ መጻሕፍቶችን የማጠናከር ስራ እየተሰራ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

ቤተመጻህፍቱ የሚያስፈልጋቸውን ግብኣት በማሟላት አገልግሎት እንዲሰጡ ለማስቻል ከባለ ድርሻ አካላት ጋር በትብብር እየተሰራ መሆኑን ጠቁመዋል።

መልካም ሰብእናን ለመገንባትና በምክንያታዊነት የሚያምኑ ወጣቶችን ለማፍራት የንባብ ባህልን ማዳበር አስፈላጊ ነው የሚሉት አቶ አብርሃም ወጣቶችና ሌላውም የህብረተሰብ ክፍል ወደ ማዕከላቱ በመምጣት እንዲያነቡ ጥሪ አስተላልፈዋል።

በድጋፉ ላይ የስፖርት ማህበረሰቡን በመወከል የተገኘው የአዲስ አበባ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ምክትል ፕሬዚዳንት አትሌት መልካሙ ተገኝ በበኩሉ ዛሬ ከተደረገው ድጋፍ በተጨማሪ በቀጣይ ታዋቂ አትሌቶችን በማስተባበር ለአብርሆት ቤተ መጻሕፍት ድጋፍ ለማድረግ ማቀዳቸውን ተናግሯል።

አትሌት መልካሙ አክሎም ከስፖርት ቤተሰቡ በተጨማሪ ማንኛውም ሰው ወደ ቤተመጻሕፍቱ በመምጣት እውቀት እንዲገበይና ድጋፍ እንዲያደርግ ጥሪ አስተላልፏል።

በአዲስ አበባ ከተማ 113 በላይ የወጣቶች የሰብዕና ማእከላት እንደሚገኙ ከከተማዋ ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም