ለአንድ ሳምንት የሚቆይ የንባብ ሳምንት በአብርሆት ቤተ መጽሐፍት ተጀመረ

3

ግንቦት 24 ቀን 2014 (ኢዜአ) የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ባህልና ኪነ ጥበባት ቢሮ የተዘጋጀ ለአንድ ሳምንት የሚቆይ የንባብ ሳምንት በአብርሆት ቤተ መጽሐፍት ተጀመረ፡፡

የአዲስ አበባ ባህልና  ኪነ ጥበባት ቢሮ ሃላፊ ዶክተር ሂሩት ካሳው፤ በተለያዩ ጊዜያት የሚካሄዱ የንባብ ሳምንታትና አውደ ርዕዮች የዜጎችን የማንበብ ፍላጎት ለማሳደግ እገዛ እያደረጉ መሆኑን ገልጸዋል።

በተያዘው ዓመት ለሁለተኛ ጊዜ በተዘጋጀው የንባብ ሳምንትና አውደ ርዕይ ፕሮግራም ላይ በከተማዋ ከሚገኙ 26 ቤተ መጽሐፍትና ከ22 በላይ የመጻህፍት መደብሮች ተሳታፊ መሆናቸውን ጠቁመዋል፡፡

ለአንድ ሳምንት በሚቆየው በዚህ መርሐ ግብር የወጣቶችን የማንበብ ፍላጎት ለማሳደግ በታዋቂ ደራሲያን የማነቃቂያ ፕሮግራሞች እንደሚከናወኑም ገልጸዋል፡፡

የከተማ አስተዳደሩ የወጣቶችን የንባብ ባህል ለማሳደግ በሁሉም ክፍለ ከተሞች የሚገኙ የተለያዩ ቤተ መጻህፍትን ያደራጃል ብለዋል፡፡

የብሄራዊ ቤተ-መዛግብትና ቤተ መጽሐፍት ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር ይኩኖአምላክ መዝገቡ፤ በከተማዋ የሚገኙ በርካታ ቤተ መጽሐፍት በበቂ ሁኔታ አልተደራጁም ብለዋል፡፡

በመሆኑም በከተማዋ ቤተ- መጽሐፍትን ለማስፋፋትና በዘመናዊ መንገድ ለማደራጀት የባህልና ኪነጥበባት ቢሮና መሰል ተቋማት ቅድሚያ ሰጥተው ሊሰሩበት ይገባል ብለዋል፡፡