ለአገራዊ ምክክሩ ውጤታማነት የዜጎች ሁለንተናዊ ተሳትፎና እገዛ እንዲጠናከር ተጠየቀ

105

ግንቦት 24/2014/ኢዜአ/ የኢትዮጵያ ሴት ፖለቲከኞች የጋራ ጥምረት፤ ለአገራዊ ምክክሩ ውጤታማነት የዜጎች ሁለንተናዊ ተሳትፎና እገዛ እንዲጠናከር ጠየቀ።

ጥምረቱ በወቅታዊ አገራዊ ጉዳይ ላይ በዛሬው እለት መግለጫ የሰጠ ሲሆን ባለ ስምንት ነጥብ የአቋም መግለጫም አውጥቷል።

የኢትዮጵያ ሴት ፖለቲከኞች የጋራ ጥምረት  ሰብሳቢ ነቢሃ መሀመድ፤ በሰጡት መግለጫ ኢትዮጵያ እንደ ሀገር እያጋጠሟት ካሉ ፈተናዎች ለመላቀቅ ሁሉን አካታች ብሔራዊ ምክክር ያስፈልጋል ብለዋል።

ለዚህም ስኬት የዜጎች ሁለንተናዊ ተሳትፎና እገዛ ወሳኝ በመሆኑ ሁሉም የድርሻውን እንዲወጣ ጠይቀዋል።

አሸባሪው ህወሐት ቀደም ሲል የፈጸመው ወረራ በአገሪቱ ፖለቲካ ላይ ቀውስ ማስከተሉን በመግለጫው አስታውሰው ከእንድህ አይነት አገር አፍራሽ እንቅስቃሴ ሊታቀብ ይገባዋል ብለዋል።

ቡድኑ የጣለውን ጠባሳ ለመቀልበስ ኢትዮጵያዊያን በአንድነት በመቆምና በጋራ በመምከር ለሰላማቸው መረጋገጥ  የበኩላቸውን ሚና ሊወጡ ይገባል ብለዋል፡፡

ኢትዮጵያ እያጋጠሟት ካሉ ፈተናዎች ለመላቀቅ ሁሉን አካታች ብሔራዊ ምክክር ማድረግ ዋነኛው መፍትሄ መሆኑን ጠቅሰው ለተግባራዊነቱ ጥምረቱ የድርሻውን እንደሚወጣ አረጋግጠዋል።

የሰላም እጦት ሲከሰት በግንባር ቀደም ተጎጂ የሚሆኑት ሴቶችና ህፃናት ናቸው ያሉት ሰብሳቢዋ

ሴቶች ለሰላም መረጋገጥ ግንባር ቀደም ተሳታፊ ሊሆኑ ይገባል ነው ያሉት።

ለአገራዊ ምክክሩ መሳካት መላ ኢትዮጵያዊያን፣ መንግስት፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ የሀይማኖት ተቋማት፣ የሀገር ሽማግሌዎችና ሌሎች ባለድርሻ አካላት የበኩላቸውን አስተዋጽኦ ሊያደርጉ ይገባል ብሏል የጥምረቱ መግለጫ።

የኢትዮጵያ ሴት ፖለቲከኞች የጋራ ጥምረት ዋና ፀሀፊ መሊሀ ጅሀድ፤ የህግ የበላይነትን ለማረጋገጥ በመንግስት የተለያዩ እርምጃዎች መወሰዳቸው አወንታዊ ምልከታ እንዳላቸው ገልጸዋል።

በዚህ ሂደት ግን የተጠርጣሪዎች አያያዝ ሂደትና የእስረኞች አያያዝ ህጋዊነትን የተከተለና ሰብአዊ መብትን ባከበረ መልኩ መሆኑ እንዳይዘነጋ አሳስበዋል።

የፖለቲካ ፓርቲዎችም ይሁኑሌሎች አካላት የሚያወጧቸው መግለጫዎችና የሚያደርጓቸው ንግግሮች የግጭትና የልዩነት ምክንያት እንዳይሆኑ ሊጠነቀቁ እንደሚገባም ተናግረዋል።

በተለያዩ ምክንያቶች የተፈናቀሉ ወገኖች ሰብአዊ ድጋፍ ማድረግ ጊዜ ሊሰጠው የማይገባ ጉዳይ መሆኑንም ጠቅሰዋል።

በወንጀል ተጠርጥረው የተያዙ ዜጎች የተፋጠነ ፈትህ እንዲያገኙ ማድረግ፤ የኑሮ ውድነቱን የሚያባብሱ ህገ-ወጥ ተግባራትን ተከታትሎ እርምጃ መውሰድ የመንግስት ትልቅ ሃላፊነት መሆኑንም ገልጸዋል።

ከተመሰረተ ከሁለት አመታት በላይ የሆነው የኢትዮጵያ ሴት ፖለቲከኞች የጋራ ጥምረት ከ300 በላይ አባላት እንዳሉት መረጃዎች ይጠቁማሉ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም