በአዲስ አበባ በአስራ አንድ ወራት ከ5 ነጥብ 3 ቢሊዮን ብር በላይ የልማት ስራና የበጎ ፍቃድ አገልግሎት ተከናውኗል

3

ግንቦት 24 ቀን 2014 (ኢዜአ) በአዲስ አበባ በአስራ አንድ ወራት በማህበረሰቡ ተሳትፎ ከ5 ነጥብ 3 ቢሊዮን ብር በላይ የልማት ስራና የበጎ ፍቃድ አገልግሎት ተግባር መከናወኑን የከተማ አስተዳደሩ የህብረተሰብ ተሳትፎና በጎ ፈቃድ ማስተባበሪያ ኮሚሽን ገለፀ።

የኮሚሽኑ ኮሚሽነር አስፋው ተክሌ፤ በከተማ አስተዳደሩ የበጎ ፈቃድና የማህበረሰብ ተሳትፎ የተከናወኑ ተግባራትን በተመለከተ ለኢዜአ ገልጸዋል።

በማብራሪያቸውም ባለፉት አስራ አንድ ወራት የኮብልስቶን ንጣፍና ጥገና፣ የጸጥታ ጥበቃ ስራ፣ የኮሙዩኒቲ ፖሊሲንግና የጥበቃ ማማዎች ስራ፣ አነስተኛ መፀዳጃ ቤቶችና ድልድዮች ግንባታ እና ሌሎችም ስኬታማ ተግባራት መከናወናቸውን ተናግረዋል።

የተለያዩ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ጫና ያለባቸውን የህብረተሰብ ክፍሎች የመደገፍ የበጎ ፍቃድ ስራ በህብረተሰቡ ተሳትፎ መከናወኑንም አስረድተዋል።

ከአዲስ አበባ መንገዶች ባለስልጣንና ከኮብልስቶን ማስተባበሪያ ፅህፈት ቤት ጋር በመሆን የመንገድ መሰረተ ልማት ዝርጋታ እየተሰራ መሆኑንም ገልፀዋል።

በኮብል ስቶን ንጣፍ 72 ኪሎ ሜትር ለማከናወን ታቅዶ 79 ኪሎ ሜትር ማከናወን እንደተቻለም ጠቅሰዋል።

በጥራት ችግርና በረጅም ጊዜ አገልጋሎት የተበላሹ 93 ኪሎ ሜትር የኮብልስቶን መንገዶችን ለመጠገን ታቅዶ 87 ነጥብ 6 ኪሎ ሜትር መሰራቱን ጠቁመው ቀሪው 5 ኪሎ ሜትር ክረምቱ ከመግባቱ በፊት ይጠናቀቃል ብለዋል።

በማህበረሰቡ ተሳትፎ 38 የኮሙዩኒቲ ፖሊሲንግ ፅህፈት ቤቶች እና 79 የጋራ መፀዳጃ ቤቶች ግንባታ መከናወኑንም ኮሚሽነሩ ገልጸዋል።

በእነዚህ ስራዎች በገንዘብ፣ በጉልበትና በቁሳቁስ ተደምሮ ከ513 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት ስራ መከናወኑን ገልጸው የአምናው ተመሳሳይ ወቅት አፈፃፀም 322 ሚሊዮን ብር እንደነበር አስታውሰዋል።

በከተማዋ የኑሮ ውድነት ጫና ሊያደርስባቸው ይችላል ተብለው ለተለዩ ከ370 ሺህ በላይ ዜጎች ከሚያዝያ 1 እስከ ሰኔ 30 የሚቆይ የማዕድ ማጋራት መርሃ ግብር መጀመሩንም አንስተዋል።

በዚህ ዙሪያ ከአምና ክረምት አንስቶ እስካሁን ከ1 ነጥብ 7 ሚሊዮን በላይ ወገኖችን ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉንም አስታውሰዋል።

በበጎ ፍቃድ ከ4 ነጥብ 8 ቢሊዮን ብር በላይ በማሰባሰብ የማዕድ ማጋራት፣ የቤት እድሳትና ሌሎችም ስራዎች መከናወናቸውን ኮሚሽነሩ ተናግረዋል።

በአጠቃላይ ባለፉት 11 ወራት ህብረተሰቡን ያሳተፉ ከ5 ነጥብ 3 ቢሊዮን ብር በላይ የሚገመቱ የተለያዩ  የልማትና የበጎ ፍቃድ ተግባራት መከናወናቸው ተገልጿል።

በቀጣይ ወራትም የማዕድ ማጋራት፣ ከተማ ማስዋብ፣ የአረንጓዴ ልማት ስራዎችና ሌሎች ተግባራት እንደሚከናወኑ ጠቁመው የማህበረሰቡ ተሳትፎ እንድጠናከር ጠይቀዋል።