የሠሜኑን ጦርነት ተከትሎ ወንጀሎችና የሰብዓዊ መብት ጥሰት የፈጸሙ አካላትን ተጠያቂ የማድረጉ ሥራ ዓለም አቀፍ መርሆዎችን ተከትሎ እየተከናወነ ነው

121

ግንቦት 24 ቀን 2014 (ኢዜአ) በሠሜኑ የኢትዮጵያ ክፍል የተቀሰቀሰውን ጦርነት ተከትሎ የተለያዩ ወንጀሎችና የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን የፈጸሙ አካላትን ተጠያቂ የማድረጉ ሥራ ዓለም አቀፍ መርሆዎችን ተከትሎ እየተከናወነ መሆኑን የሚኒስትሮች የጋራ ግብረ ኃይል ገለጸ።

ፍትህ ሚኒስቴር በጦርነቱ ምክንያት የተፈጸሙ ወንጀሎችና የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን ለመመርመርና ድጋፍ ለማድረግ የተቋቋመውና ጉዳዩን በበላይነት የሚያስፈጽመው የሚኒስትሮች የጋራ ግብረ ኃይል ያከናወናቸውን ተግባራት አስመልክቶ ዛሬ ለአውሮፓ አገራት አምባሳደሮች ገለጻ አድርጓል።

May be an image of 12 people, people sitting, people standing and indoor

የግብረ ኃይሉ ጽህፈት ቤት ኃላፊ ዶክተር ታደሰ ካሳ በዚሁ ጊዜ እንደገለጹት ጦርነቱን ተከትሎ በማንኛውም ወገን የተፈጸሙ ወንጀሎችና የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች እየተመረመሩ ነው።

የምርመራ ሥራውን የሚያካሂዱ ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት የተውጣጡ ከ150 በላይ የዘርፉ ባለሙያዎች መዋቀራቸውን ገልጸው ባለሙያዎቹ ለጊዜው በአፋርና በአማራ የምርመራ ሥራቸውን መጀመራቸውን ነው ያስረዱት።

በመሆኑም ቡድኑ በሰሜን ሸዋ፣ በአማራ ክልል የኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳደር፣ በኮምቦልቻ ከተማ፣ በደሴ ከተማ፣ በጃማና ወረኢሉ አካባቢዎች፣ በወልዲያና አካባቢው፣ በላሊበላ ከተማ፣  በዋግ ኸምራ ዞንና  በአፋር ክልል መሰማራቱን ጠቁመዋል።

የሚኒስትሮች ግብረ ኃይል በሁሉም ቡድኖች ተፈጽመዋል የተባሉ ወንጀሎችንና የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን የተመለከቱ የሰውና የሰነድ ማስረጃዎች የማሰባሰብ ሥራ ውስጥ መሆኑን ገልጸዋል።

በአፋርና በአማራ ክልል የተፈጸሙ ወንጀሎችንና የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን ለመመርመር የሚያስችል የምርመራ ዲዛይን መዘጋጀቱንም አክለዋል።   

በተመሳሳይ በወልቃይት ጠገዴና በቃፍታ ሁመራ ወረዳዎች ተፈጽሟል የተባሉ የመብት ጥሰቶችን የሚመረምር ቡድን መዋቀሩን ጠቅሰው የሁኔታዎች መሟላትን ተከትሎ ወደ ሥራ የሚገባ ይሆናል ብለዋል።

በሌላ በኩል በአክሱም ከተማ በመከላከያ የሠራዊት አባላት ተፈጽመዋል የተባሉትን ግድያዎች በተመለከተ ምርመራው የመከላከያ ሠራዊት ከትግራይ መውጣቱን ተከትሎ መቋረጡን ጠቁመው ይህም በቀጣይ ምቹ ሁኔታ ሲፈጠር ዳግም ይጀመራል ነው ያሉት።  

በትግራይ ኃይሎች በማይካድራ የተፈጸሙትን የጅምላ ግድያዎች የተመለከቱ መረጃዎች ተሰባስቦ የፍርድ ሂደት መጀመሩንም ነው የገለጹት።

በተጓዳኝም በመከላከያ ሚኒስቴር ወታደራዊ ፍርድ ቤት ሥር ጉዳያቸው የታየና በእንጥልጥል ያሉ የወንጀል ጉዳዮች መኖራቸውን ተናግረዋል።   

በአጠቃላይ የሚኒስትሮች ግብረ ኃይል በተፈጸሙ ወንጀሎችና የመብት ጥሰቶች ተጠያቂነትን ለማስፈን የሚያደርጋቸው ተግባራት ዓለም አቀፍ መርሆዎችን በተከተለ መንገድ እየተከናወኑ መሆኑን ተናግረዋል።

በተለይም በኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብትና የመንግሥታቱ ድርጅት የሰብዓዊ መብት አቻ ተቋም የጋራ ምርምራ ውጤትና ምክረ ኃሳቦችን ተከትሎ የሚከናወን መሆኑንም ነው ያነሱት።   

የሚኒስትሮች ግብረ ኃይል ያዋቀራቸው የምርመራ ቡድኖች ዓለም አቀፍ ደረጃዎችን የተከተሉ እንዲሆኑ ለማስቻል የአቅም ግንባታ ሥልጠና እየተሰጠ መቆየቱም ተጠቁሟል።

ግብረ ኃይሉ የሚያከናውናቸው የምርመራ ሥራዎች በዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ዘንድ ቅቡልነትን ማግኘታቸውን ጠቁመው ይህም ትልቅ ፖለቲካዊ ጠቀሜታ እንዳለው ገልጸዋል።  

የምርመራ ቡድኑ በቀጣይ መረጃ ባሰባሰበባቸው አካባቢዎች ክስ ወደ መመሥረት ሂደት የሚገባ ሲሆን ምርመራ ባልተካሄደባቸው አከባቢዎች የምርመራ ሥራውን እንደሚያካሂድ ዶክተር ታደሰ ገልጸዋል።   

ግብረ ኃይሉ በተለይም በአማራና በአፋር ክልሎች ያካሄዳቸው የምርመራ ሥራዎች በአመዛኙ እየተጠናቀቁ መሆኑን ጠቁመው በቀጣይ ሪፖርቱ ይፋ ይሆናል ብለዋል።    

ተቀማጭነታቸውን በአዲስ አበባ ያደረጉ የአውሮፓ አባል አገራት አምባሳደሮች የሚኒስትሮች ግብረ ኃይል ያቀረበውን ገለጻ ተከትሎ ውይይት አድርገዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም