ከተሞች የራሳቸውን ገቢ በማሳደግ ለዜጎች ኑሮ መሻሻልና የስራ እድል ፈጠራ በትኩረት መስራት አለባቸው - ኢዜአ አማርኛ
ከተሞች የራሳቸውን ገቢ በማሳደግ ለዜጎች ኑሮ መሻሻልና የስራ እድል ፈጠራ በትኩረት መስራት አለባቸው

ግንቦት 24 ቀን 2014 (ኢዜአ) ከተሞች የራሳቸውን ገቢ በማሳደግ ለዜጎች ኑሮ መሻሻል፣ ለኢንቨስትመንትና ለስራ እድል ፈጠራ በትኩረት ሊሰሩ እንደሚገባ የከተማና መሰረተ ልማት ሚኒስትሯ ጫልቱ ሳኒ አስገነዘቡ።
ሁለተኛው አገር አቀፍ የከንቲባዎችና የግሉ ዘርፍ ኮንፈረንስ "ተግዳሮትን የሚቋቋሙ ከተሞች በኢንተርፕርነርሺፕ የተቃኘ ተግባር ለከተሞች መነቃቃት እና ዕድገትና የከንቲባዎች ሚና'' በሚል መሪ ሀሳብ በአዲስ አበባ እየተካሄደ ይገኛል።
የከተማና መሰረተ ልማት ሚኒስትር ጫልቱ ሳኒ፤ በመድረኩ ላይ በመገኘት ባስተላለፉት መልእክት ከተሞች የራሳቸውን ገቢ በማሳደግ ለዜጎች ኑሮ መሻሻል በትኩረት እንዲሰሩ አሳስበዋል።
ከንቲባዎች ከተሞችን በዕውቀት፣ በልምድና ወቅቱን በዋጀ ጠንካራ ራዕይ በመምራት ኢንቨስትመንትን በመሳብ ለስራ ዕድል ፈጠራ ከግሉ ዘርፍ ጋር በጋራ መስራት አለባቸው ብለዋል።
ከተሞች ለነዋሪዎች ምቹ ውብና ጽዱ እንዲሆኑ ማድረግ የመንግስት የትኩረት አቅጣጫ መሆኑን ጠቅሰው ለዚህ ስኬት ከንቲባዎች ትልቅ ሃላፊነት ያለባቸው መሆኑን አስገንዝበዋል።
መንግሥት ከምንግዜውም በላይ ለከተሞች ዕድገትና መስፋፋት ለዜጎች ህይወት መሻሻል በትኩረት እየሰራ ይገኛል ብለዋል።
ከተሞች ለነዋሪዎቻቸው ምቹ፣ ሰላማዊና ያደጉ እንዲሆኑ የግሉ ዘርፍ ተሳትፎ ወሳኝ መሆኑንም ጠቅሰዋል።
የንግድና ቀጠናዊ ትስስር ሚነስትር ገብረመስቀል ጫላ፤ በበኩላቸው የግሉ ዘርፍ በንግድና ኢኮኖሚ ልማት እንቅስቃሴ ውስጥ የሚጠበቅበትን ሚና እንዲወጣ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
የንግድ ስራ ለመጀመር ከዚህ በፊት በአማካይ 32 ቀናትና 11 ሂደቶችን ማለፍ ይጠይቅ የነበረው ወደ 5 ቀናትና 4 ሂደቶች ዝቅ ማድረግ መቻሉንም ተናግረዋል።
የንግድ ግንኙነትና ትስስርን በማጎልበት የገበያ መዳራሻዎችን ይበልጥ በማሳደግ በዓለም አቀፍና በአህጉራዊ የንግድ እድሎችና ውድድሮች ላይ በመሳተፍ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የዓለም ንግድ ድርጅት አባልነት ድርድር እየተደረገ መሆኑንም ጠቁመዋል።
በንግድ ስርዓት ውስጥ የሚታየውን ህገ-ወጥነት ለመከላከል በጋራ በመስራት ችግሩን መፍታት ያስፈልጋል ብለዋል።
የኢትዮጵያ ንግድ ዘርፍ ማኅበራት ፕሬዝዳንት ኢንጅነር መላኩ አዘዘው፤ ምክር ቤቱ መንግሥትና የግሉ ዘርፍ ለአገሪቱ ኢኮኖሚ ዕድገት የበኩላቸውን እንዲወጡ እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
የግሉ ዘርፍ ከመንግስት አካላት የሚጠበቀውን አገልግሎት ፍጥነት እና ጥራት እንዲያገኙ የሚያስችል ትስስር ለመፍጠርና ለማህበረሰቡ የተሻለ አገልግሎት ለመስጠት የኮንፍረንሱ መዘጋጀት አስፈላጊ ስለመሆኑም ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ ከተሞች የትብብር መድረክ ዋና ዳይሬክተር አንዱዓለም ጤናው፤ በበኩላቸው ፎረሙ የንግዱ ዘርፍ ተዋናዮች ከንቲባዎች ጋር በመገናኘት በቀጣይ የልማት ስራዎች እንዲሳተፉ ለማድረግ ያለመ መሆኑን አስረድተዋል።
በከተሞች ኢንቨስት በማድረግ የስራ ዕድል ለመፍጠር እና የከተሞችን ገቢ ለማሳደግም በስፋት እንዲሳተፉ ያግዛል ብለዋል።
ለሁለት ቀናት በሚካሄደው መድረክ በስራ ዕድል ፈጠራ፣ በንግድ መሰረተ ልማት፣ የከተማ አስተዳደር እና የአፍሪካ ነፃ ቀጠና ጉዳዮች ላይ ምክክር እንደሚደረግ ይጠበቃል።
በመድረኩ ከፍተኛ የመንግሥት ስራ ኃላፊዎች፣ የከተሞች ከንቲባዎች፣ የንግዱ ዘርፍ ማኅበረሰብ አባላት እና ሌሎችም ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል።