በጋምቤላ ክልል የዲማ ወረዳን ከክልሉ ርዕሰ ከተማ የሚያገናኘው የአስፋልት መንገድ ግንባታ እየተፋጠነ ነው

244

ጋምቤላ፤ ግንቦት 24/2014(ኢዜአ) በጋምቤላ ክልል የዲማ ወረዳን ከክልሉ ርዕሰ ከተማና ከወረዳዎች ጋር የሚያገናኘው የ72 ኪሎ ሜትር የአስፋልት መንገድ ግንባታ እየተፋጠነ መሆኑን የኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር አስታወቀ።

ፕሮጀክቱ የዲማ ወረዳን ከክልሉ ዋና ከተማና ከሌሎች ወረዳዎች ለማገናኘት ከፉኝዶ -ጊሎ እና ከአኩላ- አቻኛ ዲማ ራድ መገንጠያ በሚል እየተሰራ ያለው የ154 ኪሎ ሜትር የአስባልት መንገድ አካል መሆኑ ተመላክቷል።

የፉኝዶ- ጊሎ የመንገድ ፕሮጀክት ተቆጣጣሪ ኢንጂነር ግዛቸው ጌቴ እንዳሉት በፕሮጀክቱ ከሚከናወነው የ72 ኪሎ ሜትር የመንገድ ግንባታ 42 ከመቶው ተጠናቋል።

ፕሮጀክቱ ከዲማ ወረዳ ወደ ጋምቤላ ከተማ ለመምጣት ተጎራባች ክልሎችን ለማቋረጥ የሚደረገውን 430 ኪሎ ሜትር ጉዞ በግማሽ በማሳጠር ከጋምቤላ ከተማና ከወረዳዎች ጋር በቀጥታ የሚያገናኝ መሆኑን አስረድተዋል።

በተጨማሪ መንገዱ ወርቅን ጨምሮ በወረዳው ያለውን የማዕድን ሀብት ጥቅም ላይ ለማዋል የሚያስችልና  ለግብርና ኢንቨስትመንት ምቹ ሁኔታን የሚፈጥር ነው ብለዋል።

በቻይናው ''ሪልዎይ ሰቨንዝ ግሩፕ'' ተቋራጭ የፕሮጀከቱ ተጠሪ ሚስተር ጎ ቦውን ፕሮጀክቱን በተያዘለት የጊዜ ሰሌዳ ለማጠናቀቅ እየሰሩ መሆናቸውን ገልጸዋል።

የአኝዋሃ ዞን ምክትል አስተዳዳሪ አቶ ኡጁሉ ኝጌዎ በበኩላቸው በዞኑ ከሚገኙት ወረዳዎች መካከል ከክልሉ ርዕሰ ከተማ ብሎም ከሌሎች ወረዳዎች ጋር የሚያገናኝ መንገድ የሌለው የዲማ ወረዳ መሆኑን ጠቁመዋል።

በዚህም ምክንያት ከወረዳው ተነስቶ ወደ ክልሉ ዋና ከተማ ለመሄድ የደቡብና የኦሮሚያ ክልሎችን አቆራርጦ መሄድ የግድ እንደሚል ገልጸው፤ ይህም ለከፍተኛ እንግልትና ወጪ እንደሚዳርግ ተናግረዋል።

በኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር እየተካሄደ ያለው ግንባታ የአካባቢውን የመንገድ ችግር እንደሚያቃልልና  ግንባታውም በጥሩ ፍጥነት ላይ እየተካሄደ እንደሚገኝ ጠቁመዋል።

የመንገዱ ግንባታ ወደ ዲማ ለመሄድም ሆነ ለመምጣት በሌሎች ክልሎች በኩል ሲያደርጉት የነበረውን ጉዞ እንደሚያሰቀርላቸው የገለጸው ደግሞ የአካባቢው ነዋሪ ወጣት ሀብታሙ ኡማን ነው።  

በክልሉ ከአኩላ- አቻኛ ራድ መገንጠያ የሚገነባው 82 ኪሎ ሜትር የሚረዝም መንገድ በግንባታ ላይ እንደሚገኝ ከአስተዳደሩ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

ከፉኝዶ -ጊሎ እና ከአኩላ- አቻኛ ዲማ ራድ መገንጠያ በሚል እየተሰራ ያለው የመንገድ ፕሮጀክት ግንባታ በ2017 እንደሚጠናቀቅ ተገልጿል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም