በክልሉ የተካሄደው ሕግ የማስከበር ዘመቻ የጠላትን ሴራ ያከሸፈ ነው

5

ባህርዳር ግንቦት 24/2014 (ኢዜአ) በአማራ ክልል የተካሄደው ሕግ የማስከበር ዘመቻ የጠላትን ሴራ ያከሸፈ ነው ሲል የክልሉ መንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ አስታወቀ።

የክልሉ መንግሥት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ኃላፊ አቶ ግዛቸው ሙሉነህ ዛሬ በወቅታዊ ጉዳይ ላይ መግለጫ ሰጥተዋል።

ኃላፊው በመግለጫቸው መንግሥት በክልሉ ባለፉት ሶስት ሳምንታት ያካሄደው ሕግ የማስከበር ዘመቻ ውጤታማ በመሆኑ በክልሉ ህገ ወጥ የጥይት ተኩስ፣ ዝርፊያና ስርቆት ቀንሷል ብለዋል።

ሕግ የማስከበር ዘመቻው የጠላትን ሴራ ያከሸፈና ውጤታማ በመሆኑ ኅብረተሰቡ በሰላም ወጥቶ እንዲገባ ማስቻሉን ገልጸዋል።

በዘመቻው ክልሉን እና ኢትዮጵያን ለማፍረስ ሲንቀሳቀሱ የነበሩ በርካታ ተጠርጣሪ ግለሰቦች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ተናግረዋል።

በቁጥጥር ስር ከዋሉት መካከል ከጠላት ተልዕኮ ተቀብለው በህቡ ሲንቀሳቀሱ የቆዩ፣ በግድያና  በማህበራዊ ሚዲያ ህዝብን ከህዝብ በማጋጨት የተጠረጠሩ ግለሰቦች እንደሚገኙበት ገልጸዋል።

“ሥርዓት አልበኛ ሆኖ የሚንቀሳቀስ ማንኛውም ተጠርጣሪ ከህግ ማምለጥ እንደማይችል የተካሄደው የህግ ማስከበር ዘመቻ ማሳያ ነው” ብለዋል።

የሕግ ማስከበር ዘመቻው ውጤታማና የጠላትን ሴራና ፍላጎት ያከሸፈና ህብረተሰቡ በሰላም ወጥቶ እንዲገባ ያስቻለ መሆኑን አቶ ግዛቸው አስታውቀዋል።

የክልሉ ሕዝብ ከመንግሥት ጎን በመሆን ዘመቻው ውጤታማ እንዲሆን አስፈላጊውን ሁሉ ድጋፍ እያደረገ መሆኑን ጠቅሰው፣ ለዚህም  በክልሉ መንግሥት ስም ምስጋና አቅርበዋል።

የተጀመረው ሕግ የማስከበር ሥራ ተጠናክሮ ስለሚቀጥል ህብረተሰቡ ድጋፉን አጠናክሮ እንዲቀጥልም አቶ ግዛቸው ጥሪ አቅርበዋል።