የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር በዳውሮ ዞን በድርቅ ለተጎዱ ወገኖች የእለት ደራሽ ምግብ ድጋፍ አደረገ

169

ግንቦት 24/2014 (ኢዜአ)  የውሃ እና ኢነርጂ ሚኒስቴር በደቡብ ምእራብ ኢትዮጵያ ክልል ዳውሮ ዞን በድርቅ ለተጎዱ ወገኖች የ3 ሚሊዮን ብር ግምት ያለው የዕለት ደራሽ ምግብ ድጋፍ አደረገ።

የውሃ እና ኢነርጂ ሚኒስትሩ ዶክተር ኢንጅነር ሀብታሙ ኢታፋ፤ ድጋፉን በስፍራው በመገኘት አስረክበዋል።

የተደረገው ድጋፍ በአካባቢው በድርቁ ጉዳት ለደረሰባቸው ወገኖች ደራሽ የሚሆን 593 ኩንታል የበቆሎ ዱቄት እና 550 ሊትር ዘይት መሆኑም ተገልጿል።

በዳውሮ ዞን አምስት ወረዳዎች ከ186 ሺህ በላይ ሰዎች በድርቅ ሳቢያ ለችግር መዳረጋቸውን መረጃዎች አመላክተዋል።

በድርቁ ሳቢያ እስካሁን በተለይም የቁም እንስሳት በመኖ እጥረት ለከፍተኛ ችግር መጋለጣቸውም ታውቋል።

በመሆኑም ድርቁ በአካባቢ ላደረሰው ጉዳት እልባት ለመስጠት ሰብአዊ ድጋፍ ማድረግ በማስፈለጉ ሚኒስቴሩ የቻለውን ማድረጉ ተገልጿል።

በቀጣይም ሌሎች ተቋማትና ድጋፍ ሰጭ ድርጅቶች እገዛ በማድረግ ሰብአዊነታቸውን እንዲያሳዩ ይጠበቃል።

የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር በዞኑ ድጋፍ ሲያደርግ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ዶክተር ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ፣ የዳውሮ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ዶክተር መኩሪያ በላቸውን ጨምሮ ሌሎችም የስራ ሃላፊዎች ተገኝተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም