በምስራቅ ባሌ ዞን በ7 የበልግ አብቃይ ወረዳዎች የተከሰተውን ተምች ለመቆጣጠር ጥረት እየተደረገ ነው

227

ጎባ ግንቦት 24/2014(ኢዜአ) በኦሮሚያ ክልል ምስራቅ ባሌ ዞን የበልግ ሰብል አብቃይ በሆኑ ሰባት ወረዳዎች ላይ የተከሰተው ተምች የከፋ ጉዳት ሳያደርስ ለመቆጣጠር ጥረት እየተደረገ መሆኑን የዞኑ ግብርና ጽህፈት ቤት ገለጸ፡፡

ተምቹን በባህላዊና በኬሚካል ርጭት ለመቆጣጠር ጥረት እያደረጉ መሆኑን የአከባቢው አርሶ አደሮቹ ተናግረዋል፡፡

የዞኑ ግብርና ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ሹክሪ ጣሃ ለኢዜአ እንደገለጹት ተምቹ የተከሰተው በዞኑ  የበልግ ሰብል አብቃይ በሁኑ ሰባት ወረዳዎች ውስጥ ነው፡፡

ተምቹ  በበልጉ  በለማ 7ሺህ ሄክታር  የበቆሎ፣ ዘንጋዳና የጤፍ   ሰብሎች ላይ መከሰቱን አመልክተዋል፡፡

እየለማ ባለው ሰብል ላይ የከፋ ጉዳት እንዳይደርስ አርሶ አደሩና የግብርና ባለሙያዎች በባህላዊ  ዘዴና በኬሚካል ርጭት ለመቆጣጠር ጥረት እያደረጉ እያደረጉ እንደሚገኙ ገልጸዋል፡፡

አቶ ሹክሪ እስከ አሁን በባህላዊና 2ሺህ ሊትር ኬሚካል በመርጨት በ3 ሺህ ሄክታር እርሻ ላይ የተከሰተውን ተምች  መቆጣጠር መቻሉን ገልጸዋል፡፡

የተቀናጀ የተምች ቁጥጥር ስራ ተጠናክሮ መቀጠሉን የጠቆሙት ኃላፊው ተጨማሪ የኬሚካል አቅርቦት እንዲደርስ  ለክልሉ ግብርና ቢሮ ጥያቄ መቅረቡን ጠቁመዋል፡፡

አርሶ አደሩ የተከሰተውን ተምች በባህላዊ ዘዴ መቆጣጠር እንደሚቻል በግብርና ባለሙያዎች የሚሰጠውን ሙያዊ ምክር ተግባራዊ በማድረግ የቁጥጥር ስራውን አጠናክሮ እንዲቀጥል መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡

በቁጥጥር ስራው እየተሳተፉ ከሚገኙ የጊኒር ወረዳ አርሶ አደሮች መካከል ሀሰን በከር በሰጡት አስተያየት የዝናብ ስርጭት በሚፈለገው መጠን በሌለበት ጊዜ ተምቹ መከሰቱ በቡቃያው ላይ የሚያደርሰው ጉዳት ከፍተኛ ነው ብለዋል፡፡

"የቁጥጥር ስራው ውጤታማ እንዲሆን በባህላዊ መልኩ እያደረግን ከምንገኘው ጥረት በተጓዳኝ በኬሚካል ርጭት ልንታገዝ ይገባል" ነው ያሉት፡፡

"አርሶ አደሮች በኩታ ገጠም በመደራጀታችን በኅብረት አረም ለማረምና ተባይ ለመከላከል ረድቶናል" ያሉት ደግሞ ሌላው የልማቱ ተሳታፊ ማህሙድ አብደላ ናቸው፡፡

በምስራቅ ባሌ ዞን በዘንድሮ የበልግ የምርት ወቅት ከ122 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በተለያዩ ሰብሎች ለምተው እንክብካቤ እየተደረገለት መሆኑን ከዞኑ ግብርና ጽህፈት ቤት የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም