የዲጂታል ዲፕሎማሲውን በተደራጀና ተቋማዊ በሆነ መልኩ በመምራት የኢትዮጵያን ጥቅም በዘላቂነት ማስጠበቅ ይገባል

147

ግንቦት 24 ቀን 2014 (ኢዜአ) የዲጂታል ዲፕሎማሲውን በተደራጀና ተቋማዊ በሆነ መልኩ በመምራት የኢትዮጵያን ጥቅም በዘላቂነት ማስጠበቅ እንደሚገባ የማህበራዊ ሚዲያ አንቂው ወጣት ሱሌማን አብደላ ተናገረ።

ከቴክኖሎጂ እድገት ጋር ተያይዞ የዓለም ነባራዊ ሁኔታዎች በፍጥነት እየተቀያየሩ ሲሆን፤ በተለይ የዲጂታል ሚዲያ መስፋፋት የአገራትንም ሆነ የዜጎችን መደበኛ መስተጋብር ቀይሯል፡፡

በዚህም አገራት ከመደበኛው የተግባቦት ስርዓት ባሻገር ዲጂታል ዲፕሎማሲን ዋነኛው የጥቅም ማስከበሪያ ማእቀፍ አድርገው እየተጠቀሙ ይገኛሉ፡፡

በሳኡዲ አረቢያ የሚኖረው የማህበራዊ ሚዲያ አንቂ ወጣት ሱሌማን አብደላ ከኢዜአ ጋር በበይነ-መረብ ባደረገው ቆይታ በሰሜኑ የሀገሪቷ ክፍል የተቀሰቀሰውን ጦርነት ተከትሎ በኢትዮጵያ ላይ ከፍተኛ የዲፕሎማሲ ጫና ሲደረግ መቆየቱን አስታውሷል፡፡

ዓለም አቀፍ የመገናኛ ብዙሃን ተቋማትና ሌሎች ግለሰቦች በዲጂታል ሚዲያ ጭምር የተሳሳተ መረጃ በማሰራጨት በኢትዮጵያ ላይ ከፍተኛ ጫና ሲያደርጉ መቆየታቸውን ገልጿል፡፡

በዚህም በተለያዩ አገራት የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን በተናጠልም ቢሆን የኢትዮጵያን እውነት ለማሳወቅ ከፍተኛ ጥረት ማድረጋቸውን አንስቶ፤ የ#በቃ ንቅናቄን በዚህ ረገድ ለአብነት አንስቷል፡፡

በሌላው ዓለም የዲጂታል ዲፕሎማሲ እንቅስቃሴ በተደራጀና በተቀናጀ መልኩ የሚሰራበት እንደሆነ የሚገልጸውወጣት ሱሌማን፤ በተለይ ግብጽና ሌሎች አገራት ይህን ተሞክሮ በስፋት እንደሚጠቀሙበት አንስቷል።

በመሆኑም በቀጣይ ሊያጋጥሙ የሚችሉ ፈተናዎችን ከወዲሁ በመገንዘብ ዲጂታል ዲፕሎማሲውን በተደራጀና ተቋማዊ በሆነ መንገድ መምራት ይገባል ነው ያለው፡፡

በዚህም የዩኒቨርሲቲና ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የተውጣጡ ምሁራንና ባለሙያዎችን ባሳተፈ መንገድ ዲጂታል ዲፕሎማሲውን ለማጎልበት መሰራት እንደሚገባ ተናግሯል፡፡

በኢትዮጵያ ላይ በተጀናጀና በተናበበ መንገድ የሚሰራጩ  ሀሰተኛ መረጃዎችን በጋራ መመከት እንደሚገባም ነው ያነሳው፡፡

በቀጣይ የኢትዮጵያን እውነት ለዓለም በማሳወቅ ረገድ የጀመረውን ጥረት አጠናክሮ እንደሚቀጥልም አረጋግጧል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም