በሀገሪቱ የተለያዩ ከተሞች የኤሌክትሪክ ኃይል ማስተላለፊያ ምሰሶዎችንና ትራንስፎርመሮችን የማሻሻል ስራ ይካሄዳል

57

አሶሳ ግንቦት 23 / 2014 (ኢዜአ)በ100 ሚሊዮን ዶላር ወጪ አዲስ አበባን ጨምሮ በተለያዩ የሀገሪቱ ከተሞች ያረጁ የኤሌክትሪክ ኃይል ማስተላለፊያ ምሰሶዎችንና ትራንስፎርመሮችን የማሻሻል ስራ እንደሚያካሂድ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ገለጸ፡፡

አገልግሎት በፕሮጀክቱ ላይ ከባለድርሻ አካላት ጋር ዛሬ በአሶሳ ውይይት አድርጓል፡፡

በአገልግሎቱ የዲስትሪቢዩሽንና ሪሃብሊቴሽን ፕሮግራም ኃላፊ አቶ ተፈራ ደርቤ እንደገለጹት ከዓለም ባንክ በተገኘ 100 ሚሊዮን ዶላር ብድር በተለያዩ ከተሞቹ ባለ15 ኪሎ ቮልት ሃይል ማስተላለፊያ ምሰሶዎችንና ትራንስፎርመሮችን ደረጃ የማሻሻል ፕሮጀክት ይከናወናል፡፡

ፕሮጀክቱ ለበርካታ አመታት ያገለገሉና ያረጁ የሃይል ተሸካሚ ምሰሶዎች እያስከተሉ ያለውን ከፍተኛ የኃይል ብክነት በመቀነስ ለከተሞቹ ተጨማሪ  ኃይል ለማቅረብና አዳዲስ ደንበኞችን ተጠቃሚ ለማድረግ ያስችላል ብለዋል፡፡

በከተሞቹን የሚስተዋለውን የሃይል እጥረት በማቃለል የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴዎችን እንደሚያጠናክርም ነው ኃላፊው የጠቀሱት፡፡

በሚቀጥሉት ሁለት ዓመታት ውስጥ በሚተገበረው ፕሮጀክት በከተሞቹ አገልግሎት በመስጠት ላይ ያሉና ያረጁ መካከለኛ የኤሌክትሪክ ኃይል ተሸካሚ ምሰሶዎችን በኮንክሪት እንዲተኩ ይደረጋል ብለዋል።

በፕሮጀክቱ ያረጁ የኤሌክትሪክ ትራንስፎርመሮች የመቀየርና ተጨማሪ አዳዲስ የመትከል ስራ እንደሚሰራ ተናግረዋል፡፡

ፕሮጀክቱን ለማስጀመር የአማካሪ ድርጅቶች ቅጥር እየተፈጸመ መሆኑንም አቶ ተፈራ ገልጸዋል።

በአካባቢ ጥበቃና ማህበራዊ ደህንነት ላይ የሚያደርሰውን ጉዳት ለመቀነስ እያካሄደ ያለው የዳሰሳ ጥናት በመጠናቀቅ ላይ እንደሚገኝም  ተናግረዋል፡፡

ለፕሮጀክቱ የሚያስፈልጉ ግብዓቶችን ግዥ ለመፈጸም በቅርቡ ዓለም አቀፍ ጨረታ እንደሚወጣ ኃላፊው አስታውቀዋል፡፡

ፕሮጀክቱ ከአዲስ አበባ በተጨማሪ አሶሳ፣ ነቀምቴ፣ አምቦ፣ ሱሉልታ፣ ደብረ ብርሃን፣ አሰላ፣ ዲላ፣ ሆሳዕናና ጅግጅጋ ከተሞችን እንደሚያካትት ጠቁመዋል፡፡

በውይይ ከተሳተፉት መካከል አቶ ኡመር መሐመድ እንዳሉት ፕሮጀክቱ በአሶሳ ከተማ በተደጋጋሚ የኃይል መቆራረጥና የትራንስፎርመር ብልሽት ምላሽ እንደሚሰጥ እምነታቸውን ገልጸዋል፡፡

የቴሌኮሙኒኬሽን፣የመንገድ፣ የውሃና ሌሎች አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ቅንጅታዊ አሰራር ለፕሮጀክቱ ተፈጻሚነት ባላቸው ሚና ትኩረት እንዲሰጡም ጠይቀዋል፡፡

በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ጽህፈት ቤት ሥራ አስፈጻሚ አቶ ካሳሁን ከበደ ፕሮጀክቱ ስኬት ጽህፈት ቤቱ  የባለድርሻ አካላትን ተሳትፎ ለማጠናከር ጥረት እንደሚያደርግ ገልጸዋል፡፡