በድርጅቱ የተገነቡት የመጠለያ ድንኳኖች የተፈናቃዮችን ችግር ያቃልላሉ

6

ሰቆጣ ግንቦት 23/2014 (ኢዜአ) ልማት ለሰላም ድርጅት (ዲፒኦ) በዋግ ኽምራ ብሄረሰብ አስተዳደር ዞን ወለህ የመጠለያ ጣቢያ የገነባቸው ድንኳኖች የተፈናቃዮችን የመጠለያ ችግር እንደሚያቃልል የዞኑ አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ጽህፈት ቤት ገለጸ።

ድርጅቱ የገነባቸውን 20 የመጠለያ ድንኳኖችን ለዞኑ አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ጽህፈት ቤት አስረክቧል።
የፅህፈት ቤቱ የቅድመ ማስጠንቀቂያ ምላሽ ቡድን መሪ ወይዘሮ ዝናሽ ወርቁ ለኢዜአ እንደገለጹት በድርጅቱ የተሰሩት የመጠያ ድንኳኖች የተፈናቀሉ ወገኖችን የመጠለያ ችግር የሚያቃልሉ ናቸው።

መጭው የክረምት ወቅት ከመሆኑ ጋር ተያይዞም የተፈናቀሉ ወገኖች የሚገጥማቸውን የመጠለያ ችግር ለማቃለል ድንኳኖቹ የሚኖራቸው ጠቀሜታ የላቀ መሆኑንም ተናግረዋል።
ድርጅቱ ለተፈናቀሉ ወገኖች እያደረገ ላለው ድጋፍም ምስጋና አቅርበው የተፈናቀሉ ወገኖችን ወደ ተሰሩት የመጠለያ ድንኳኖች የማስገባቱ ስራ መጀመሩንም አስረድተዋል።
የተፈናቃይ ወገኖች ቁጥር በየጊዜው እየጨመረ በመምጣቱ የመጠለያ ድንኳኖች እጥረት ማጋጠሙን ጠቅሰው ሌሎች ግብረሰናይ ድርጅቶችም መሰል ድጋፎችን እንዲያደርጉ ወይዘሮ ዝናሽ ጥሪ አቅርበዋል

የድርጅቱ መሃንዲስ አቶ ያሬድ ዘሪሁን በበኩላቸው በጦርነቱ ምክንያት ከቤት ንብረታቸው ለተፈናቀሉ ወገኖች መጠለያ የሚሆኑ ድንኳኖችን በመጠለያ ጣቢያው እየገነባ መሆኑን ተናግረዋል።
.
በዞኑ ከቤት ንብረታቸው ተፈናቅለው በወለህ የመጠለያ ጣቢያ ለሚገኙ ተፈናቃዮች መጠለያ ድንኳኖቹን ሰርተው ማስረከባቸውን ገልፀዋል።
የተሰሩት የመጠለያ ድንኳኖችም 1 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር ወጭ እንደተደረገባቸው ጠቅሰው፤ ለ600 ተፈናቃይ ወገኖች በመጠለያነት ያገለግላሉ ብለዋል።
ድርጅቱ ከመጠለያ ድንኳን ግንባታ በተጨማሪም በፅፅቃ ለሚገኙ 400 ተፈናቃይ ወገኖች ለስድስት ወራት የቤት ኪራይ የሚሆን ወደ 2 ሚሊዮን ብር የሚጠጋ ድጋፍ ማድረጉንም አስታውቀዋል።

ከፃግብጅ ወረዳ ተፈናቅለው በመጠለያ ጣቢያው የሚገኙት ወይዘሮ አበቡ ጌታሁን በአሸባሪው ህወሓት ከቤት ንብረታቸው ተፈናቅለው አምስት ልጆቻቸውን ይዘው ወደ ሰቆጣ መምጣታቸውን ገልጸዋል።
መጠለያ ጣቢያው ቀደም ሲል ከነፋስና ዝናብ የሚከላከል ባለመሆኑ ልጆቻቸው ለከፋ የጤና ችግር ሲዳረጉ እንደቆዩ ገልጸው አሁን የነበረባቸው ችግር እንደተቃለለላቸው ተናግረዋል።
መጪው ክረምት ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ለመጠለያ የተሰሩት ድንኳኖች ዝናብና ብርድን መቋቋም የሚያስችሉ በመሆኑ ያለሰቀቀን ከነልጆቼ ለመጠለል አመች ነው ብለዋል።
ሌላኛው ተፈናቃይ አቶ ዓለሙ ቸኮለ በበኩላቸው በመጠለያ ጣቢያው አዲስ የተሰሩ የመጠለያ ድንኳኖች የተፈናቃዮችን ችግር ታሳቢ ያደረጉ መሆናቸውን ተናግረዋል።
የመጠለያ ቹንኳኖች በአባ ወራ ደረጃ የተከፋፈሉ መሆናቸው ደግሞ ለመኖሪያ አመች እንደሆኑም አስረድተዋል።

ከዞኑ የተለያዩ አካባቢዎች ከቤት ንብረታቸው የተፈናቀሉ ከ88 ሺህ በላይ ወገኖች እንደሚገኙ ከዞኑ አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤት የተገኘው መረጃ ያመለክታል።