በሲዳማና ኦሮሚያ አጎራባች አካባቢዎች የሚከሰቱ ግጭቶችን በማስቆም የሠላምና የልማት ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ እየተሰራ ነው

ግንቦት 23 ቀን 2014 (ኢዜአ) በሲዳማና ኦሮሚያ ክልል አጎራባች አካባቢዎች የሚፈጠሩ ግጭቶችን በማስቆም የህዝቡን የሠላምና የልማት ተጠቃሚነት በዘላቂነት ለማረጋገጥ እየተሰራ መሆኑ ተመላከተ።

በሁለቱ ክልሎች አዋሳኝ በሆኑ አንዳንድ አካባቢዎች አልፎ አልፎ ይከሰቱ የነበሩ ግጭቶችን በዘላቂነት ለማስወገድ የሀገር ሽማግሌዎች፣ አባገዳዎች፣ የጎሳ መሪዎች፣የሁለቱም ህዝቦች አመራርና ባለድርሻ አካላት የተገኙበት የውይይት መድረክ በሐዋሳ ከተማ ተካሂዷል።

የሲዳማ ክልል ሠላምና ፀጥታ ቢሮ ኃላፊ አቶ አለማየሁ ጢሞቲዎስ በመድረኩ መክፈቻ ላይ ባደረጉት ንግግር፣ ሁለቱ ወንድማማች ህዝቦች ትስስራቸው የጠነከረ መሆኑን በመግለጽ ለዘመናት አብሮ የመኖር እሴት ያለውን የሁለቱን ክልሎች ህዝብ ለማጋጨትና ጉዳት ለማድረስ ብዙ ሙከራ መደረጉን አስታውሰዋል።

ከለውጡ ወዲህ ግጭቶችን ከማረም አኳያ በህዝቡና በሁለቱ ክልሎች አመራሮች ቁርጠኝነት ከፍተኛ ስራ በማከናወን አብሮነትንና አንድነትን በማስፈን ጠንካራ የህዝብ ለህዝብ ትስስር መፍጠር መቻሉን አስታውቀዋል።

በአስተዳደር ወሰን፣በግጦሽ መሬት፣ በውሃና በሌሎችም ምክንያቶች አልፎ አልፎ ግጭቶች እንደሚከሰቱ አመልክተው በተለይ የሁለቱን ማህበረሰብ ሰላም የማይፈልጉ አካላት በሚለኩሱት እሳት ወጣቶች ወደ ስህተት ውስጥ እንዳይገቡ በመካላከል ረገድ የሀገር ሽማግሌዎች፣ አባገዳዎች እና የጎሳ መሪዎች ተሳትፎአቸውን እንዲያጠናክሩ ታስቦ የውይይት መድረኩ መዘጋጀቱን አስታውቀዋል።

በአጎራባች አካባቢዎቻችን አልፎ አልፎ የተፈጠሩ ግጭቶችን በማስቆም ህዝቡን የሰላም እና የልማት ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በጋራ እየተሰራ መሆኑንም ነው ያስታወቁት።

የኦሮሚያ ክልል አስተዳደርና ፀጥታ ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ኃይሌ ጉርሜሳ በበኩላቸው ምንም እንኳ ቀጠናው የትርምስ ማእከል እንዲሆን የሚሰሩ አካላት ቢኖሩም ከህዝቡ ጋር በተሰራው ስራ አጥጋቢ ውጤት ተመዝግቧል ብለዋል።

በአሁኑ ወቅት በሁለቱ አጎራባች አካባቢዎች በተለያዩ ምክንያቶች ሲፈጠሩ የነበሩ ግጭቶች አብዛኛዎቹ መፈታታቸውን በመጠቆምም በቀጣይ የሁለቱን ህዝቦች ግንኙነት የሚያጠናክሩ ስራዎችን ማስቀጠል አስፈላጊ መሆኑን አንስተዋል።

ከምክክር መድረኩ ተሳታፊዎች መካከል የምእራብ አርሲ ዞን አባገዳ ነጌሶ ገመቹና አጠቃላይ የሲዳማ ጎሳ መሪ አቶ ሻምበል በላይ በሰጡት አስተያየት ለግጭት መነሻ ከሆኑት ውስጥ የመሬት ወረራ፣የአመራር ችግር እና የፀረ ሰላም ኃይሎች እንቅስቃሴ እንደሚገኙበት ጠቅሰዋል።

ለግጭት መንስዔ የሆኑት ጉዳዮች እልባት እንዲያገኙና ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍን ከመንግስት ህግ ማስከበር ተግባራት ጎን ለጎን በባህላዊ እርቅ ሥርዐት ችግሩን ለማቃለል እየተንቀሳቀሱ መሆናቸውን ተናግረዋል።

በሁለቱም በኩል ችግሩን የሚያባብሱ ጥገኛ አክቲቪስቶች፣አንዳንድ አመራሮች እና ጥቅመኛ ግለሰቦች እንዳሉ ጠቅሰው ግጭት እንዲቀሰቀስ የሚፈልጉ አካላትን መንግሥት እና ህዝብ ሊያስቆማቸው እንደሚገባ አስታውቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም