ኢትዮጵያ ያጋጠሟትን ችግሮች ተቋቁማ በርካታ የዘላቂ ልማት ግብ አመላካቾች ላይ ውጤት ማስመዝገብ ችላለች

114

ግንቦት 23/2014 (ኢዜአ) ኢትዮጵያ ያጋጠሟትን ችግሮች ተቋቁማ በርካታ የዘላቂ ልማት ግብ አመላካቾች ላይ ውጤት ማስመዝገብ መቻሏን የፕላንና ልማት ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡

ኢትዮጵያ ከሁለት ወራት በኋላ በኒዮርክ በሚካሄደው ዓለም አቀፍ የፖለቲካ መድረክ ላይ የዘላቂ ልማት ግቦች አፈጻጸም ሪፖርቷን እንደምታቀርብም ነው የተገለጸው፡፡

በዚህም ሚኒስቴሩ ለኢትዮጵያ የዘላቂ ልማት ግቦች አፈጻጸም ሪፖርት የሚሆን ግብዓት ማሰባሰቢያ መድረክ  ከባለድርሻ አካላት ጋር አካሂዷል፡፡

ሚኒስትሯ ዶክተር ፍጹም አሰፋ በዚህ ወቅት ሪፖርቱ በዋናነት በሰው ሃብት ልማት፣ በማህበራዊ፣ በኢኮኖሚያዊና በሰብዓዊ መብቶች አያያዝ ጉዳዮች ላይ ትኩረት እንደሚያደርግ ተናግረዋል፡፡

በዚህም በሪፖርቱ በስፋት የተብራሩ 17 ግቦች ተካተዋል ነው ያሉት፡፡

ኢትዮጵያ እንደ አውሮፓዊያን አቆጣጠር ከ2020 ጀምሮ በበርካታ ሰው ሰራሽና ተፈጥሯዊ ፈተናዎች ማለፏን ጠቅሰው፤ ድርቅ፣ የኮቪድ-19 ወረርሽኝ እንዲሁም በሰሜን ኢትዮጵያ የተከሰተውን ጦርነት በአብነት አንስተዋል፡፡

እነዚህ ችግሮች ለኢትዮጵያ አጠቃላይ የልማት እቅዶች አፈጻጸም ከፍተኛ ፈተና ቢፈጥሩም ይህንን በመቋቋም የተሻለ ውጤት መመዝገቡንም ተናግረዋል፡፡

ባለፉት ስድስት ዓመታትም ኢትዮጵያ በጠቅላላ አገራዊ ምርት የ7 ነጥብ 9 በመቶ እድገት ማስመዝገቡን በዚህ ረገድ አንስተዋል፡፡

የዘላቂ የልማት ግቦችን በሚመለከትም "በበርካታ አመላካቾች ውጤት ተመዝግቧል" ነው ያሉት፡፡

ከኢትዮጵያ አጠቃላይ በጀት ውስጥ 60 በመቶ የሚሆነው ለደሃ ተኮር ሥራዎች እንደሚመደቡ ጠቅሰው፤ ይህም የዘላቂ የልማት ግቦችን በማሳካት ረገድ ወሳኝ ሚና እየተጫወተ መሆኑን አብራርተዋል፡፡

በመድረኩ የተሳተፉ ባለድርሻ አካላት በሰጡት አስተያየት፤ ኢትዮጵያን ያጋጠሟት ሰው ሰራሽና ተፈጥሯዊ ችግሮች በማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተቋማት ላይ ያስከተሉት ተጽዕኖ በስፋት ሊዳሰስ እንደሚገባ ጠቅሰዋል፡፡

ድርቅን ጨምሮ በኢትዮጵያ የተከሰቱ ተፈጥሯዊ አደጋዎች የሰው ህይወት እንዳይቀጥፉ መንግሥት የወሰዳቸው እርምጃዎች ሊዳሰሱ እንደሚገባም ነው ያነሱት፡፡

ባለፉት አራት ዓመታት የጸጥታ ተቋማትን ጨምሮ በሌሎች ተቋማት ላይ የተሰሩ የሪፎርም ሥራዎች ትኩረት ተሰጥቷቸው ሊዳሰሱ እንደሚገባም ነው የገለጹት፡፡

የተለያዩ የስራ ሀላፊዎች በሪፖርት ግምገማው ላይ ባነሱት አስተያየት ይሀገሪቱን ሁለንተናዊ የለውጥ ጉዞዎች መዳሰስ አንዳለበት አንስተዋል፡፡

የገንዘብ ሚኒስትሩ አህመድ ሺዴ ለተነሱ አስተያየቶች በሰጡት ምላሽ  በመድረኩ የተነሱ ግብዓቶችን በማካተት ሪፖርቱ እንደሚጠናከር ገልጸዋል፡፡

በተጨማሪ የኢትዮጵያን እድገት ለማፋጠን የተወሰዱ የፋይናንስ ማስተካከያዎችንና ተያያዥ ጉዳዮችን በሚመለከት የተከናወኑ ተግባራት እንደሚካተቱ ጠቅሰው፤ የኢትዮጵያን ትክክለኛ ገጽታ የሚያሳይ ሪፖርት ለማቅረብ ጥረት ይደረጋል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም