የግብርና ምርታማነትን በማሳደግ ኢንዱስትሪዎች በቂ ግብዓት እንዲያገኙ ይሰራል---ዶክተር ይልቃል ከፋለ

156

ባህር ዳር(ኢዜአ)፣ግንቦት 22/2014 የግብርና ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ ኢንዱስትሪዎች በቂ ግብዓአት እንዲያገኙ በሁሉም ርብርብ በትኩረት እንደሚሰራ የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ዶክተር ይልቃል ከፋለ አስታወቁ።

ለግብርና ልማቱ በቂ በጀት በመመደብና በኢንቨስትመንት በማጠናከር በኩል ያለውን ክፍተት ለመሙላት የፋይናንስ አሰራር ሥርዓቱን የማሻሻል ሥራ እንደሚሰራም ተገልጿል።

የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ በ2014/2015 የምርት ዘመን በቅድመ ዝግጅት ወቅት በተከናወኑ ተግባራትና በቀጣይ በሚከናወኑ ሥራዎች ላይ የክልልና የዞን አመራሮች በተገኙበት በባህር ዳር ከተማ  መክክር ተካሂዷል።

ርዕሰ መስተዳድር ዶክተር ይልቃል በዚሁ ጊዜ እንዳሉት ለግብርና ልማቱ አጋዥ የሆኑ ግብዓቶችና ቴክኖሎጂዎችን  በማቅረብ  እንዲሁም  የመካናይዜሽን እርሻ  በመጠቀም ምርታማነትን ለማሳደግ አቅምን አሟጦ መስራት ይገባል።

"በተለይ ምርታማነትን በማሳደግ ለኢንዱስትሪዎች ግብዓት በበቂ ሁኔታ ለማቅረብ አመራሩና የግብርና ባለሙያው ከአርሶ አደሩ ጋር በቅንጅት ተናበው መስራት ይጠበቅባቸዋል" ብለዋል።

ዶክተር ይልቃል እንዳሉት እስካሁን ለግብርና ልማቱ ቅድሚያ ቢሰጥም ለዘርፉን በቂ በጀት በመመደብና በኢንቨስትመንት በማጠናከር በኩል ተገቢ ትኩረት አልተሰጠውም።

በቀጣይ ይህን ለመቀየር መስራት እንደሚገባ አሳስበው፣ በክልሉ የምርምር አቅም እንዲጠናከር ዩኒቨርሲቲዎችና  የግብርና ምርምር ጣቢያዎችን በበጀትና በግብዓት የመደገፍ ሥራ እንደሚሰራ ተናግረዋል።

ለዚህም የፋይናንስ  አሰራር ስርዓቱን በማሻሻል ለግብርና ልማቱ  የሚኖረውን  አስተዋጾ ለማሳደግ  የክልሉ መንግስት አስፈላጊውን ሁሉ እገዛ ያደርጋል ብለዋል።

"እንደ ሀገርም ሆነ እንደ ክልል የገጠመውን የምግብ እጥረት ተቋቁሞ ማለፍ የሚቻለው ግብርናውን ለማዘመን  በቁርጠኝነት  መስራት ስንችል ነው"  ያሉት ደግሞ በብልፅግና ፓርቲ የአማራ ክልል ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ ግርማ የሽጥላ ናቸው።

ለእዚህም አርሶ አደሩ በበቂ ሁኔታ እንዲያመርት በአመራሩ በኩል ማገዝና ማበረታት ያስፈልጋል ብለዋል።

በባለፈው ዓመት በክልሉ  የተገኘውን 120 ሚሊዮን  ኩንታል  የምርት መጠን   በ2014/2015 የመኸር የምርት ዘመን ወደ 143 ሚሊዮን ኩንታል ለማሳደግ ታቅዶ እየተሰራ  መሆኑን  የክልሉ  ግብርና ቢሮ ሃላፊ ዶክተር ሃይለማሪያም ከፍያለው ናቸው።

"የተያዘው ዕቅድ ሰፊ  ቢሆንም  ዕቅዱ  እንዲሳካ  አርሶ አደሩን  ማገዝና አስፈላጊውን  ሁሉ ሙያዊ ድጋፍ ማድረግ   ከሁሉም ባለድርሻ አካላት ይጠበቃል" ብለዋል።

በመድረኩ ላይ የተሳተፉት የምስራቅ ጎጃም ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ አብርሃም አያሌው በበኩላቸው በምርት ዘመኑ በዞኑ ለማምረት የታቀደውን 22 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ለማሳካት እየተሰራ መሆኑን  ገልጸዋል።

የታቀደውን ምርት ለማምረት  አስፈላጊው  ቅድመ  ዝግጅት  መደረጉን  ገልጸው፣ ለዚህም አመራሩና ባለሙያው ህዝቡን በቅርበት ሆነው እያነሳሱና እየደገፉ መሆኑን አመልክተዋል።

በክልሉ በ2014/2015 የመኸር  ወቅት 4 ነጥብ 8 ሚሊዮን ሄክታር  መሬት  በዘር ለመሸፈን ታቅዶ የእርሻ ስራው እየተከናወነ  መሆኑን  ከክልሉ ግብርና ቢሮ የተገኘ መረጃ ያስረዳል።

በውይይት መድረኩ የክልሉ ከፍተኛ አመራሮች፣ የዞን አስተዳዳሪዎች፣ የድርጅት ሃላፊዎች እንዲሁም የዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንቶች ተሳትፈዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም