የሸማቾች ሕብረት ሥራ ማህበራት ምርቶችን በቀጥታ ከአርሶ አደሮች የሚሸምቱበት የአሰራር ሥርዓት እንዲመቻች ጠየቁ

639

ግንቦት 23/2014/ኢዜአ/ የሸማቾች ሕብረት ሥራ ማህበራት የግብርና ምርቶችን በቀጥታ ከአርሶ አደሮች የሚሸምቱበት የአሰራር ሥርዓት እንዲመቻች ጠየቁ።

የሸማች ሕብረት ሥራ ማኅበራት የግብርና እና የኢንዱስትሪ ምርቶችን ለማኅበረሰቡ በተመጣጣኝ ዋጋ በማቅረብ በእሑድ ገበያ በተመረጡ አካባቢዎች በማገበያየት ላይ ይገኛሉ።

በዚህም በአዲስ አበባ የኑሮ ውድነት ችግርን ለማቃለል በሚደረገው ጥረት ማህበራቱ የድርሻቸውን በመወጣት ላይ ይገኛሉ።

በዚሁ እንቅስቃሴ ዙሪያ የኢዜአ ሪፖርተር የልደታ፣ አራዳ እና ጉለሌ ክፍለ ከተሞች የሸማች ሕብረት ሥራ ማህበራት ኃላፊዎችን አነጋግሯል።

የእሑድ ገበያ በመጀመሩ በማኅበረሰቡ ተጠቃሚነት ላይ የሚታይ ውጤት ማስመዝገቡን የሚናገሩት ኃላፊዎቹ፤ በተለይም የግብርና ምርቶች የግብይት ሰንሰለት መርዘም እንቅፋት መሆኑን ጠቅሰዋል።

ለሸማቹ ማኅበረሰብ አሁን ከሚቀርብበት የተሻለ ዋጋ ለመሸጥ ምርት ከአርሶ አደሩ እስከ ሕብረት ሥራ ማህበራቱ እስከሚደርስ በግብይት ሰንሰለቱ በደላሎች እየተስተጓጎለና ተጨማሪ ወጪ እያስከተለ መሆኑን ተናግረዋል።

በመሆኑም የሕብረት ሥራ ማህበራቱ የግብርና ምርቶችን በቀጥታ ከአርሶ አደሮች የሚሸምቱበት የአሰራር ሥርዓት እንዲመቻችላቸው ጠይቀዋል።

ከአዲሱ ገበያ ሸማች ሕብረት ሥራ ማህበር አቶ መሳይ አበበ በሰጡት አስተያየት "የገበያ ሰንሰለቱን ለማሳጠር  እየተሰራ ያለው ስራ በቂ አይደለም፤ የምንቀበለው ቀጥታ ከገበሬውም ሳይሆን ሰንሰለቱ በጣም ረጅም ነው፤ የሚያጥርበት ሁኔታ ቢኖር ዋጋውም የተወሰነ ለውጥ ይኖራል ብዬ አስባለሁ"ብለዋል፡፡

ቀጥታ ገበሬው አምጥቶ ለእኛ ቢያስረክበን ለህብረተሰቡ አሁን  ካለው ዋጋ ባነሰ ዋጋ መሸጥ እንችላለን " ያሉት ደግሞ ከልደታ ሸማች ህብረት ስራ ማህበር አቶ ተስፋዬ ወቹ ናቸው፡፡

ከአራዳ ፋና ሸማች ሕብረት ሥራ ማህበር አቶ አሸብር በየነ በበኩላቸው የሸማች ማህበራት የግብይት ሰንሰለት ማጠር እንዳለበት አመልክተዋል፡፡

የኢትዮጵያ ሕብረት ሥራ ኮሚሽን ኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር አያልሰው ወርቅነህ፤ የግብይት ሰንሰለቱን ለማሳጠር የተለያዩ የመፍትሔ አማራጮችን በመተግበር ላይ እንገኛለን ብለዋል።

በተለይም በከተሞች ሸማቾች ላልተገባ ወጪ እንዳይዳረጉ እና አምራቾችም ተጠቃሚ እንዲሆኑ የግብይት ሰንሰለቱን በማሳጠር አምራችና ሸማችን በቀጥታ ለማገበያየት እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም