ጉዳት ለደረሰባቸው ዜጎች የሥነ-ልቦና ድጋፍ የሚሰጡ ባለሙያዎችን የማብቃት ሥራ ተጠናክሮ ይቀጥላል

96

ግንቦት 23/2014/ኢዜአ/ በተፈጥሯዊና ሰው ሠራሽ አደጋዎች ጉዳት ለደረሰባቸው ዜጎች የሥነ-ልቦና ድጋፍ የሚሰጡ ባለሙያዎችን የማብቃት ሥራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ገለጸ።

በግጭትና በተፈጥሯዊ አደጋ ጉዳት ለደረሰባቸው ወገኖች የሥነ-ልቦና ድጋፍ ለሚሰጡ ባለሙያዎች ሥልጠና በደብረ ብርሃን ከተማ ትላንት ተጀምሯል።

ለአምስት ቀናት በሚቆየው በዚሁ የሥልጠና መርኃ-ግብር በማኅበራዊ፣ በጤና፣ በትምህርትና በሌሎች ዘርፎች የተሰማሩ 300 ባለሙያዎች ተሳታፊ ሆነዋል።  

ሥልጠናው በቀጣይም በኮምቦልቻ፣ በወልዲያና በሰቆጣ ከተሞች በተመሳሳይ የሚሰጥ ሲሆን፤ በድምሩ 1 ሺህ 200 ባለሙያዎች ይሰለጥናሉ ነው የተባለው።   

የሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አየለች እሸቴ እንደገለጹት፤ የሚደርስባቸውን የሥነ-ልቦና ጫና ለመቀነስ እየተሰራ ነው።

የሚሰጠውም የሥነ-ልቦና ድጋፍ ጥራቱን የጠበቀና የዜጎችን ችግር በመሰረታዊነት እንዲፈታ ለማድረግ ሥልጠናው መዘጋጀቱን ገልጸዋል።   

ሰልጣኞች የወሰዱትን ልምድ ማኅበረሰቡን እንዲያግዙ ሚኒስቴሩ እስከ ታች ድረስ ባለው መዋቅር  ክትትልና ድጋፍ ያደርጋል ብለዋል።

በቀጣይም ችግር ባጋጠማቸው በሌሎች የአገሪቱ አካባቢዎች ሥልጠናዎችን ለመስጠት ሚኒስቴሩ ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር እየሰራ መሆኑን ጠቁመዋል።

ሚኒስትር ዴኤታዋ ከዚህ ቀደም 270 ለሚሆኑ ባለሙያዎች የአሰልጣኞች ሥልጠና ተሰጥቶ ኅብረተሰቡን እንዲያግዙ የማድረግ ሥራ መሠራቱን አስረድተዋል።

የኢትዮጵያ ሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር መሳይ ኃይሉ በበኩላቸው፤ ሰልጣኞች ያገኙትን እውቀትና ክህሎት ተጠቅመው የሚያገለግሉትን ማኅበረሰብ ሊደግፉ እንደሚገባ ተናግረዋል።

ሥልጠናው የሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ከጤና ሚኒስቴርና ከመንግሥታቱ ድርጅት ዓለም አቀፍ የሕጻናት ድንገተኛ ፈንድ (ዩኒሴፍ) ጋራ በመተባበር ነው የተዘጋጀው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም