ኮካኮላ ኩባንያ በሰበታ ከተማ ያስገነባው ፋብሪካ ተመረቀ

151

ግንቦት 23 ቀን 2014 (ኢዜአ)ኮካኮላ ኩባንያ በ100 ሚሊዮን ዶላር ወጪ በሰበታ ከተማ ያስገነባው ፋብሪካ ተመረቀ፡፡

ፋብሪካው የኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ አቶ መላኩ አለበል እና የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሽመልስ አብዲሳን ጨምሮ የተቋሙ የስራ ኃላፊዎች በተገኙበት ነው የተመረቀው።

ኩባንያው ላለፉት ስድስት አስርት-ዓመታት በኢትዮጵያ ኢንቨስት አድርጎ እየሰራ የሚገኝ ሲሆን፤ ከ30 ሺህ ለሚበልጡ ዜጎች በቀጥታና በተዘዋዋሪ የስራ እድል መፍጠሩም ተመላክቷል፡፡

የኢንዱስትሪ ሚንስትሩ አቶ መላኩ አለበል በዚሁ ወቅት ድርጅቱ ባለፉት 62 ዓመታት በኢንዱስትሪ ዘርፍ የማይተካ ሚና እንዳበረከተ ተናግረዋል፡፡

ሴቶችን በመደገፍ እንዲሁም ትምህርት ቤቶችን በመገንባት ማህበራዊ ኃላፊነቱን እየተወጣ መሆኑንም እንዲሁ፡፡

መንግስት በኢንዱስትሪ ዘርፍ ያሉ ማነቆዎችን በመፍታት ዘርፉን ለማጎልበት እየሰራ እንደሚገኝም ተናግረዋል፡፡

May be an image of 5 people, people standing and suit

የኦሮሚያ ክልል ፕሬዝደንት ሽመልስ አብዲሳ በበኩላቸው በክልሉ ኢንቨስትመንትን ለማበረታታት የተሰሩ ስራዎች ውጤት እያስመዘገቡ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ክልሉ ኩባንያው እያከናወናቸው ላሉ የልማት ስራዎች የሚጠበቅበትን ድጋፍ እንደሚያደርግም አረጋግጠዋል፡፡

በኢትዮጵያ የኮካኮላ ኩባንያ ማኔጂንግ ዳይሬክተር ዳሬል ዊልሰን፤ ድርጅቱ ባለፉት አምስት ዓመታት ከ300 ሚሊዮን ዶላር በላይ ወጭ በመመደብ የተለያዩ የማስፋፋፊያ ስራዎች እያከናወነ መሆኑን ጠቅሰው፤ ዛሬ የተመረቀው ፕሮጀክትም የዚሁ አካል መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በሰበታ ከተማ ዛሬ የተመረቀው ፋብሪካ የኮካኮላ ኩባንያው 5ኛው ቅርንጫፍ መሆኑም ተገልጿል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም