የመጣንበትን የትምህርት ዓላማ ብቻ ለማሳካት ሌት ተቀን እንሰራለን-የወሎ ዩኒቨርሲቲ አዲስ ገቢ ተማሪዎች

87

ደሴ፤ ግንቦት 22/2014 (ኢዜአ) የግል አጀንዳቸውን ለማስፈጸም በሚፈልጉ አካላት ሳይታለሉ የመጡበትን የትምህርት ዓላማ ብቻ ለማሳካት እንደሚንቀሳቀሱ የወሎ ዩኒቨርሲቲ አዲስ ገቢ ተማሪዎች ተናገሩ።

ጉዳት ደርሶበት የነበረው የወሎ ዩኒቨርሲቲ ጥገና ተደርጎለት 3 ሺህ 915 አዲስ ገቢ ተማሪዎችን  ከትላንት ጀምሮ እየተቀበለ ነው።

ከተማሪዎች መካከል ከሐረሪ ክልል የመጣው ተማሪ አብዱ አደም ለኢዜአ እንደገለጸው የአብሮነት፣ የፍቅርና የሰላም ተምሳሌት ወደ ሆነው ወሎ በመምጣቱ ደስተኛ ነው።

ቀደም ሲል ጥፋት ያነገቡ አካላት የግል ጥቅማቸውን ለማሳካት ተማሪዎችን በተለያዩ ነገሮች እየደለሉ መጠቀሚያ ያደርጓቸው እንደነበር አስታውሷል።

 በቀጣይ በዩኒቨርሲቲ ቆይታው የመጣበትን የትምህርት ዓላማ ብቻ ለማሳካት ሌት ተቀን ጠንክሮ እንደሚሰራ ገልጾ፤  ''ከሌሎችም ጋር በመተሳሰብ አብሮነቴን አጠናክራለሁ" ብሏል።

ከአፋር ክልል የመጣው ተማሪ ሁማድ ዋልለ በበኩሉ "ተማሪዎች  ሰላማችንን ጠብቀን ለመማር መዘጋጀት አለብን" ብሏል።

''የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት ተጠብቆ የቆየው አባቶቻቸን ህብረታቸውን በመጠበቃቸው ነው'' ያለው ተማሪው፤ እኛም በትምህርት ቆይታችን የአባቶቻችንን አንድነትና አብሮነት በተግባር ማሳየት አለብን ብሏል።

''በትምህርታችን ውጤታማ መሆን ከእኛ ይጠበቃል'' ያለችው ደግሞ ከአማራ ክልል ደብረ ብርሃን ከተማ የመጣችው ተማሪ የምስራች አካሉ ናት።

የራሳቸው አጀንዳ ለማስፈጸም በሚፈልጉ አካላት ሳትታለል ትምህርቷን ብቻ ጠንክራ በመማር ዓላማዋን ለማሳካት ሌት ተቀን እንደምተጋም ተናግራለች።

ዩኒቨርሲቲውና የአካባቢው ማህበረሰብ በጋራ ያደረጉላቸው አቀባበል የባይተዋርነት ስሜት እንዳይሰማት ያደረጋት መሆኑንም ገልጻለች።

ልጃቸውን ለማድረስ ወደ ወሎ ዩኒቨርሲቲ የመጡት አቶ አካሉ ዘውዴ በበኩላቸው ተማሪዎች የሌሎች መጠቀሚያ በመሆን ራሳቸውን፣ ወላጆቻቸውንና ሀገራቸውን ለስጋትና ለአደጋ እንዳይዳርጉ መክረዋል፡፡

የወሎ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶክተር መንገሻ አየነ በበኩላቸው ዩኒቨርሲቲው በአሸባሪው ህወሓት ከፍተኛ ውድመት ቢደርስበትም በቅንጅት በተደረገ ርብርብ መልሶ መቋቋሙን ተናግረዋል።

በአሁኑ ወቅትም  3 ሺህ 915 አዲስ ገቢ ተማሪዎችን በቂ ዝግጅት በማድረግ እየተቀበሉ መሆኑንም አመልክተዋል።

ተማሪዎችን ደሴ እና ኮምቦልቻ ከተሞች በሚገኙ ሁለት የዩኒቨርሲቲው ካምፓሶች እየተቀበሉ መሆናቸውን አመልክተው፤ የተማሪዎችን ምዝገባ በሁለት ቀናት ውስጥ በማጠናቀቅ የመማር ማስተማር ስራው እንደሚጀመርም ተናግረዋል።

የአካባቢው ማህበረሰብ በወሎ እንግዳ አቀባበል ባህል መሰረት ተማሪዎችን እየተቀበለ መሆኑን የጠቆሙት ዶክተር መንገሻ፣ "ተማሪዎች ትኩረታቸው ትምህርት ላይ ብቻ እንዲሆን በቅንጅት እየተሰራ ነው" ብለዋል።

ተማሪዎች በተቋሙ ቆይታቸው አንድነታቸውንና ሰላማቸውን ጠብቀው ለሰላመዊ የመማር ማስተማር ሂደት የድርሻቸውን እንዲወጡም አሳስበዋል።

የወሎ ዩኒቨርሲቲ በተለያዩ የትምህርት መርሐ ግብሮች ከ26 ሺህ በላይ ተማሪዎችን  ተቀብሎ የመማር ማስተማር ስራውን እያከናወነ መሆኑን  ከዩኒቨርሲቲው የተገኘው መረጃ ያመላክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም