በክልሉ እየተካሄደ ያለው የህግ ማስከበር ስራ ግቡ የህዝብን ሰላምና ደህንነት የማስከበር ጉዳይ ነው--የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳደር

223

ባህር ዳር ፣ ግንቦት 22/2014 (ኢዜአ) በአማራ ክልል የተጀመረው የህግ ማስከበር ስራ ምንም አይነት ጫና የሌለውና ዋነኛ ግቡም የህዝብን ሰላምና ደህንነት የማስከበር ጉዳይ መሆኑን የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳደር ዶክተር ይልቃል ከፋለ ገለጹ።

ርዕሰ መስተዳደሩ በትላንትናው እለት የእርሻ ትራክተሮችን ለአርሶ አደሮች ባስረከቡበት ወቅት እንደገለጹት እየተካሄደ ያለው የህግ ማስከበር ስራ ግቡ የህዝብን ሰላምና ደህንነት ማስከበር ነው።

ሰላም የሁሉም መሰረት ነው ያሉት ርዕሰ መስተዳደሩ ያለ ሰላም ኢኮኖሚያዊ ልማቶችንና መንግስታዊ አገልግሎቶችን በተሟላ ሁኔታ ማከናወን አይቻልም ብለዋል።

ህግና ስርዓት ካልተከበረ ዜጎች የኢኮኖሚና ማህበራዊ ፍላጎታቸውን ለማሟላት ተንቀሳቅሰው መስራት እንደማይችሉ ተናግረዋል።

ህገ-ወጥነትንና ስርዓት አልበኝነትን መቆጣጠር ከተቻለ ሁሉንም ነገር ደረጃ በደረጃ ማሟላት እንደሚቻል ለአርሶ አደሮች የቀረበው ዘመናዊ የግብርና መሳሪያ ማሳያ ነው ብለዋል።

በክልሉ የተጀመረው የህግ ማስከበር ስራም ምንም አይነት ውጫዊም ሆነ ውስጣዊ ጫናና ሴራ የሌለበትና ዋናው ዓላማ የህዝብን ሰላምና ደህንነት በዘላቂነት ለማረጋገጥ መሆኑን ተናግረዋል።

የህዝብን ሰላምና ደህንነት ለማስከበር ታስቦ እየተከናወነ ላለው ጥረት ህብረተሰቡ ከመንግስት የፀጥታ መዋቅር ጎን ሆኖ ድጋፉን አጠናክሮ እንዲቀጥል አሳስበዋል።

"ፖለቲካንም መተንተን፣ ኃይልንም መጠቀም፣ነገሮችን ማስተዳደር የሁሉም ስራ ተደርጎ እየተወሰደ ነው ያሉት" በአማራ ክልል የብልጽግና ፓርቲ ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ ግርማ የሽጥላ ስርአትና ህግ ካልተከበረ ለሀገርም ሆነ ለግለሰብ እንደማይጠቅም ገልጸዋል።

አሁን ላይ በሰፈነው አንጻራዊ ሰላም የክልሉንና የህብረተሰቡን ሁለንተናዊ እድገት የሚያረጋግጡ የልማት ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑን አስታውቀዋል።

ሁሉም የህብረተሰበ ክፍል ከግል ፍላጎት በመውጣት የህግ የበላይነት የተረጋገጠበት ክልል ለመገንባት በጋራ መረባረብ እንደሚያስፈልግ ነው የተናገሩት።

በቀጣይም ልማቱን አጠናክሮ ለማሰቀጠልና ሰላምን ለማረጋገጥ ውስጣዊ አንድነትን የበለጠ ማጠናከር ይገባል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም