የፋይናንስ ተቋማት የሥራ አጥ ቁጥርን ለመቀነስ የሚያደርጉትን ድጋፍ እንዲያጠናክሩ ተጠየቀ

72

ድሬዳዋ፣ ግንቦት 22 ቀን 2014 (ኢዜአ) የፋይናንስ ተቋማት የሥራ አጥ ቁጥርን ለመቀነስ በሚደረገው ጥረት ውስጥ የሚያደርጉትን ጥረትና ድጋፍ እንዲያጠናክሩ የድሬዳዋ አስተዳደር ጠየቀ።

ዳሸን ባንክ በሥራ ፈጠራ መሠረታዊ ክህሎቶችና እውቀቶች ላይ ለ100 የድሬዳዋ ወጣቶች ስልጠና ሰጥቷል፡፡

በስልጠና መድረኩ ማጠቃለያ ላይ የድሬዳዋ ከንቲባ ተወካይና የአስተዳደሩ የመንግስት ኮሙኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ አቶ ብሩክ ፈለቀ እንደተናገሩት፤ የስራ ዕድል ፈጠራ እንቅስቃሴው በፋይናንስ ተቋማት መደገፍ አለበት።

መንግስት የሥራ አጥ ቁጥርን ለመቀነስና ማህበራዊ ችግሮችን ለማቃለል  በሚያከናውናቸው ተግባራት ውስጥ የፋይናንስ ተቋማት ሚና ወሳኝ እንደሆነም ጠቁመዋል።

የስራ ዕድል ፈጠራ ሂደቱን ስኬታማ በማድረግ የስራ አጥ ቁጥሩን ትርጉም ባለው መልኩ መቀነስ የሚቻለው ባለድርሻ አካላት ከመንግስት ጋር በመተባበር ሲሰሩ እንደሆነም አመልክተዋል።

ዳሸን ባንክና ሌሎች የፋይናንስ ተቋማት ለወጣቶች እየሰጡ ያለው የሥራ ፈጠራ እውቀትና የውድድር መንፈስ የሚበረታታና ተጠናክሮ  መቀጠል ያለበት እንደሆነ ገልጸዋል።

ዳሸን ባንክ ወጣቶችን ወደ ስራ ለማስገባት የሚያከናውነው ተግባር፣ ድርቅ የተከሰተባቸውን አካባቢዎች የመደገፍ፣ የኮቪድ-19 ወረርሽኝን ለመከላከልና ለመቆጣጠር በተደረጉ ጥረቶች የመደገፍና ሌሎች ማህበራዊ ሃላፊነትን የመወጣት ተግባሩን ማጠናከር እንዳለበት ገልጸዋል።

በተዘጋጀው የሥራ ፈጠራ ስልጠና የተሳተፉ ወጣቶች ባገኙት እውቀት ታግዘውና ከባንኩ  ጋር ትስስራቸውን አጠናክረው ህይወታቸውን ለመለወጥ በትጋት መስራት እንዳለባቸው አሳስበዋል፡፡

ሰልጣኞቹ ባንኩ ያዘጋጀላቸው ስልጠና ለሥራ ዕድል መፍጠር በር የሚከፍትና በቀጣይ ለሚያዘጋጁት የሥራ ሃሳብ መነሻ የሚያስፈልጋቸውን የገንዘብ ብድር እንዲመቻችላቸው ጠይቀዋል፡፡

የዳሸን ባንክ የድሬዳዋ ዲስትሪክት ኃላፊ ወይዘሮ ኑሪት መሀመድ ወጣቱን ወደ ሥራ እንዲገባ የማድረጉ ተግባር በመንግስት ላይ ብቻ የሚተው ሣይሆን የሁሉም ኃላፊነትና ግዴታ ነው ብለዋል፡፡

ይህን ኃላፊነት ለመወጣት ባንኩ በስድስት የአገሪቱ ከተሞች ‹የዳሸን ከፍታ የሥራ ፈጠራ ስልጠናና ውድድር መርሃ ግብር› እያካሄደ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ባንኩ ወጣቱ ወደ ሥራ እንዲገባ የተሻለ የሥራ ሃሳብ ላቀረቡ ወጣቶች ተገቢውን ብድርና ሽልማት መመቻቸቱን ገልፀዋል።

በአገሪቱ በሚከሰቱ ሰው ሰራሽና የተፈጥሮ አደጋዎች መፍትሄ ማፈላለግ ላይ የድርሻውን እየተወጣ ይገኛል ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም