በሆሮ ጉዱሩ ወለጋ ዞን ለመኸር እርሻ ከ190 ሺህ ኩንታል በላይ የአፈር ማዳበሪያ ቀረበ

42

ነቀምቴ፤ ግንቦት 22/2014 (ኢዜአ) በሆሮ ጉዱሩ ወለጋ ዞን ለ2014/2015 የምርት ዘመን ከ190 ሺህ ኩንታል በላይ የአፈር ማዳበሪያ መቅረቡን የዞኑ የሕብረት ስራ ማስፋፊያ ኤጀንሲ አስታወቀ፡፡

በዞኑ ለመኸር እርሻው 270 ሺህ 929  ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ እንደሚያስፈልግ ተመላክቷል።

የኤጀንሲው የግብርና ግብዓቶች አቅርቦትና ሥርጭት ቡድን መሪ አቶ ሀብታሙ መኮንን ለኢዜአ እንደገለጹት  በዞኑ ከነበረው የጸጥታ ችግር ጋር በተያያዘ  የአፈር ማዳበሪያ አቅርቦቱ ተጓቶ እንደነበር አስታውሰዋል።

በአሁኑ ሰዓት አንፃራዊ ሰላም በመፈጠሩ የአፍር ማዳበሪያ ለአርሶ አደሩ መድረስ መጀመሩን ተናግረዋል።

በመጓጓዝ ላይ ያለውን ሳይጨምር ከ190 ሺህ 909 ኩንታል የሚበልጥ የአፈር ማዳበሪያ ለአርሶ አደሩ መቅረቡን አስታውቀዋል፡፡

የጨፌ ቡሉቅ የገበሬዎች የሕብረት ሥራ ዩኒዬን ሥራ አስኪያጅ አቶ ታከለ ነመራ በበኩላቸው ከዞኑ ለዩኒየናቸው የደረሰውን ከ48 ሺህ 666 ኩንታል በላይ የአፈር ማዳበሪያ ለ6 ወረዳዎች መሰረታዊ ማህበራት ማድረሳቸውን ገልጸዋል፡፡

ከዞኑ የደረሳቸውን 29 ሺህ 856 ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ ለ5 ወረዳዎች መሰረታዊ ማህበራት ማድረሳቸውን የገለጹት ደግሞ የሀራጉ የገበሬዎች የሕብረት ስራ ዩኑየን ስራ አስኪያጅ አቶ ባይሳ አብዲሳ ናቸው።

ከአርሶ አደሮቹ መካከል የሆሮ ወረዳ የዶ በሪሶ ቀበሌ ነዋሪ የሆኑት አርሶ አደር ሽብሩ ለታ በሰጡት አስተያየት በአሁኑ ጊዜ 6 ሄክታር መሬት ማረሳቸውንና 1 ነጥብ 5 ሄክታር መሬት ደግሞ በበቆሎ ዘር መሸፈናቸውን ተናግረዋል፡፡

”የዘንድሮ የማዳበሪያ ዋጋ ከአርሶ አደሩ አቅም በላይ ነው” ያሉት አርሶ አደር ሽብሩ፤ 2 ነጥብ 5 ኩንታል ማዳበሪያ በ8 ሺህ 650 ብር ገዝተው በቆሎ መዝራታቸውን ገልጸዋል፡፡

የዚሁ ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር አመኑ ቦሩ በበኩላቸው እስከ አሁን 4 ሄክታር መሬት ማረሳቸውንና ግማሽ ሄክታር የእርሻ መሬታቸውን  በበቆሎ ዘር መሸፈናቸውን ተናግረዋል።

አንድ ኩንታል ማዳበሪያ በ4 ሺህ 813 ብር መግዛታቸውን የገለጹት አርሶ አደሩ፤ የአፈር ማዳበሪያ  ዋጋ ንረት እንዳሳሰባቸው ጠቁመዋል።

ባለፈው ዓመት  በ345 ብር የገዙት 12 ነጥብ 5 ኪሎ ግራም የበቆሎ ምርጥ ዘር ዋጋ በዘንድሮው ዓመት በ665 ብር ገዝተው የእርሻ መሬታቸውን በዘር ለመሸፈን መገደዳቸውን አስረድተዋል።