2 ነጥብ 7 ሚሊዮን ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ ወደ ክልሉ ገብቷል---የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ

137

ባህር ዳር፤ ግንቦት 22/2014 (ኢዜአ) በአማራ ክልል ለመኸር እርሻ የሚውል ከ2 ነጥብ 7 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ሰው ሰራሽ የአፈር ማዳበሪያ ወደ ክልሉ መግባቱን የክልሉ ግብርና ቢሮ አስታወቀ።

የቢሮው ምክትል ኃላፊ አቶ አጀበ ስንሻው ለኢዜአ እንደገለጹት በክልሉ በ2014/2015 የምርት ዘመን 4 ነጥብ 8 ሚሊዮን ሄክታር መሬት በዘር ለመሸፈን ታቅዶ የእርሻ ሥራ እየተከናወነ ነው።

እስካሁን ከ3 ሚሊዮን ሄክታር በላይ መሬትም ከአንድ እስከ ሦስት ጊዜ ታርሶ ለዘር መዘጋጀቱን ተናግረዋል።

የክልሉን አማካኝ የሰብል ምርታማነት በሄክታር ከ24 ነጥብ 5 ኩንታል ወደ 29 ነጥብ 5 ኩንታል ለማሳደግም ትኩረት በመስጠት እየተሰራ መሆኑንም ገልጸዋል።

ዕቅዱን ለማሳካት ቀደም ሲል ለክልሉ ከተገዛው 4 ነጥብ 8 ሚሊዮን ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ እስካሁን 2 ነጥብ 7 ሚሊዮን ኩንታሉ ወደ ክልሉ መድረሱን ተናግረዋል።

ከእዚህ ውስጥም ከ1 ነጥብ 2 ሚሊዮን ኩንታል የሚበልጠው ለአርሶ አደሩ መሰራጨቱን የገለጹት አቶ አጀበ፣ ቀሪው ማዳበሪያ ወደ ክልሉ እየተጓጓዘ መሆኑን አመልክተዋል።

ከውጭ 8 ነጥብ 2 ሚሊዮን ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ ለማስገባት ቢታቀድም ዓለም አቀፋዊ ሁኔታውን ተከትሎ በዓለም የማዳበሪያ ዋጋ በመናሩ በምርት ዘመኑ የታቀደውን ያህል ለማሳካት እንዳልተቻለም ተናግረዋል።

በምርጥ ዘር በኩል በምርት ዘመኑ 245 ሺህ ኩንታል የተለያየ ምርጥ ዘር ለማቅረብ መታቀዱንና እስካሁንም 212 ሺህ ኩንታል መቅረቡን አስረድተዋል።

ከቀረበው ምርጥ ዘር ከ75 ሺህ ኩንታል በላይ የሚሆነው የበቆሎ ዘር ለአርሶ አደሩ ቀድሞ መሰራጨቱንም አቶ አጀበ አስታውቀዋል።

በአፈር ማዳበሪያ አቅርቦት በኩል የነበረው ችግር ተፈቶ በአሁኑ ወቅት ማዳበሪያው ወደ ቀበሌያቸው እየገባ መሆኑን የገለጹት ደግሞ በምዕራብ ጎጃም ዞን ወንበርማ ወረዳ የማርቁማ ቀበሌ አርሶ አደር ቸኮል ታደለ ናቸው።

ዘንድሮ ማዳበሪያ ላናገኝ እንችላለን የሚል እምነት እንደነበራቸው የተናገሩት አርሶ አደሩ፤ "በአሁኑ ወቅት የማዳበሪያ ዋጋ ቢንርም 2 ኩንታል የዳፕ ማዳበሪያ ወስጃለሁ" ብለዋል።

ሁለት ሄክታር መሬታቸውን በትራክተር አርሰው በቆሎ፣ ስንዴና በርበሬ ለመዝራት ቢዘጋጁም የዝናቡ መዘግየት ሌላ ስጋት እንደሆነባቸው ተናግረዋል።

በምስራቅ ጎጃም ዞን ደብረ ኤልያስ ወረዳ ጥጃ ጠጠር ጎጥ ቀበሌ በእርሻ ኢንቨስትመንት የተሰማሩት አርሶ አደር አባትሁን ስራው በበኩላቸው፣ የተረከቡትን 17 ሄክታር መሬት ለማልማት የእርሻ ሥራ እያከናወኑ መሆኑን ተናግረዋል።

መሬቱን በበቆሎ ዘር ለመሸፈን በአሁኑ ወቅት በግብርና ቢሮ በኩል ተመዝግበው 7 ኩንታል ዳፕ ማዳበሪያ ማግኘታቸውንና በቀጣይም 5 ኩንታል ዩሪያ ለመውሰድ ተመዝግበው እየተጠባበቁ መሆኑን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም