የከተሞችን ልማትና እድገት በማፋጠን ለኑሮ ምቹ ለማድረግ እየተሰራ ነው–ሚኒስቴሩ

42

ሶዶ፣ ግንቦት 22/2014 (ኢዜአ) የከተሞች ልማትና እድገት ጊዜውን የዋጀ በማደረግ ለኑሮ ምቹ እንዲሆኑ እየተሰራ መሆኑን የከተማና መሰረተ ልማት ሚኒስቴር አስታወቀ።

የከተማ መሬት አያያዝና ፕላን አዘገጃጀት ዙሪያ ለደቡብ፣ለሲዳማና ለደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልሎች  ባለሙያዎች በወላይታ ሶዶ ስልጠና እየሰጠ ነው።

የከተማና መሰረተ ልማት ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ካሊድ አብዱረህማን እንዳሉት በከተሞች ጊዜውን የዋጀ ለውጥ በማስመዝገብ ለከተሞች ልማትና ዕድት መረጋገጥ ተግዳሮት የሆኑ ጉዳዮችን ለይቶ ለመፍታት ጥረት እየተደረገ ነው።

የከተሞችን ልማትና እድገት በማፋጠን ለኑሮ ምቹ ሆነው እንዲለሙ በሀገር ደረጃ በርካታ ተግባራት እየተከናወኑ ናቸው ብለዋል።

በሀገር ደረጃ እየተተገበረ የሚገኘው የከተማ መሬት ልማትና አስተዳደር፣ የካዳስተርና የካርታ፣ የእርግጥ ንብረት ግብይትና ግመታ (የትኛውም የመሬትና መሬት ነክ ንብረት፤ ህንፃ የሚሸጥበት ሆነ የሚገዛበትን ዋጋ የሚተምን ) እና የከተማ ፕላን ዝግጅት ሥራዎች ለውጥ እየታየባቸው መሆኑን ተናግረዋል።

ሥራዎቹ በአጭር ጊዜ የሚፈለገውን ውጤት እንዳያመጡ የስነምግባር ግድፈቶችን ለማስወገድ ሁሉም በባለቤትነት እንዲንቀሳቀስ ጠይቀዋል።

በዘርፉ አመራሩና ባለሙያው ለህብረተቡ የሚሰጣቸው አገልግሎቶችን ፍትሀዊ በማድረግ  ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ አሳስበዋል።

የከተማ መሬትን ከሌብነት በፀዳ መልኩ ለማልማትና የነዋሪዎችን የባለቤትነትና ዋስትና ለማረጋገጥ የዘርፉን የመረጃ አያያዝ በማዘመን ለውጥ እየታየ መሆኑን አስረድተዋል።

የመሬት መረጃ ስርአቱን ግልፀኝነትና ተጠያቂነት እንዲኖረው ለማስቻል ቴክኖሎጂውን የሚመጥን የሰው ኃይል ለማፍራት ትኩረት መደረጉን አቶ ካሊድ ጠቅሰዋል ።

የደቡብ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድርና የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ቢሮ ኃላፊ አቶ ተስፋዬ ይገዙ በበኩላቸው በዘርፉ የሚታዩ የልማትና የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ለማቃለል በቴክኖሎጂ የታገዘ ለማድረግ ጥረት እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል።

ዘርፉ የህግ ማዕቀፉን በተረዱ ብቃት ባላቸው ባለሙያዎች መምራት እንደሚያስፈልግ አመልክተዋል።

ዜጎች በአገልግሎት አሰጣጥ ላይ የሚያቀርቧቸውን ቅሬታዎች ለመፍታት የባለሙያዎችን አቅም መገንባት አስፈልጓል መሆኑን ገልጸው አገልግሎት ፈላጊው ጊዜና ጉልበቱን ሳያባክን ወቅቱን የጠበቀ አገልግሎት እንዲያገኝ የሚያደርገውን ጥረት ውጤታማ ማድረግ ያስፈልጋል ብለዋል።

ሰልጣኞች ከስልጠናው የሚቀስሙትን ዕውቀት ሥራውን ለማሳካት እንዲጠቀሙበትም አሳስበዋል።

ሥልጠናው ለ45 ቀናት በ16 የሙያ ደረጃዎች የሚሰጥ ሲሆን፣ በማጠናቀቂያው የደረጃ 5 የብቃት ማረጋገጫ ምዘና እንደሚሰጣቸው በመርሃ ግብር ተመላክቷል  ።