በቱሪዝም ዘርፍ የሰለጠነ በቂ የሰው ኃይል ለማፍራት የሚደረገውን ጥረት የግሉ ዘርፍ ሊደግፈው ይገባል–የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር

5

ግንቦት 22/2014 (ኢዜአ)  በቱሪዝም ዘርፍ የሰለጠነ በቂ የሰው ኃይል ለማፍራት የሚደረገውን ጥረት የግሉ ዘርፍ ሊደግፈው እንደሚገባ የሥራና ክህሎት ሚኒስትሯ ሙፈሪያት ካሚል ጥሪ አቀረቡ፡፡

የቱሪዝም ማሰልጠኛ ኢንስቲትዩት ዘጠነኛውን የእንግዳ ተቀባይነት ሳምንት “ቱሪዝም ለአብሮነት” በሚል መሪ ሃሳብ አክብሯል፡፡

በመርሃ-ግብሩ የሥራና ክህሎት ሚኒስትሯ ሙፈሪያት ካሚልን ጨምሮ ሌሎች የመንግስት የሥራ ኃላፊዎች የተገኙ ሲሆን፤ ቀኑን ምክንያት በማድረግም 100 ለሚሆኑ አቅመ ደካማ ዜጎች የማዕድ ማጋራት ተከናውኗል፡፡

ሚኒስትሯ በዚህ ወቅት እንዳሉት፤ የአሥር ዓመቱ መሪ የልማት እቅድ ከሰጣቸው ዘርፎች አንዱ ቱሪዝም ነው፡፡

በመሆኑም ዘርፉን ለማሳደግ የተለያዩ ሥራዎች እየተከናወኑ መሆኑን ጠቅሰው፤ በዘርፉ የሰለጠነ በቂ የሰው ኃይል ለማፍራት የሚደረገውን ሥልጠና በአብነት አንስተዋል፡፡

ከዚህ አኳያ የቱሪዝም ማሰልጠኛ ኢንስቲትዩት የሰለጠነ የሰው ኃይል ለማፍራት በትኩረት እየሰራ ነው ብለዋል፡፡

የቱሪዝም መጎልበት ለግሉ ዘርፍ ተጠቃሚነት ሚናው የጎላ መሆኑን የገለጹት ሚኒስትሯ፤ ባለሃብቶች በተለይ በቂ የሰው ኃይል ለማፍራት የሚደረገውን ጥረት ሊያግዙ ይገባል ብለዋል፡፡

የኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ወይዘሮ አስቴር ዳዊት በበኩላቸው፤ የቱሪዝም ዘርፍ ከኢትዮጵያ አጠቃላይ ምርት ውስጥ የዘጠኝ በመቶ ብቻ ድርሻ እንዳለው ተናግረዋል፡፡

ኢትዮጵያ ከዘርፉ የምታገኘውን ገቢ ለማሻሻል ተቋማት በቅንጅት መሥራት እንዳለባቸውም ተናግረዋል፡፡