አምስተኛው ከተማ አቀፍ የንባብ ሳምንት በአብርሆት ቤተ-መጻሕፍት ሊካሄድ ነው

117

ግንቦት 22/2014 (ኢዜአ) አምስተኛው ከተማ አቀፍ የንባብ ሳምንት ለሶስት ተከታታይ ቀናት በአብርሆት ቤተ- መጻሕፍት የሚካሄድ መሆኑን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ባህል፤ ኪነ-ጥበብና ቱሪዝም ቢሮ አስታወቀ።

የንባብ ሳምንቱ ከግንቦት 24 እስከ 26 ቀን 2014 ዓ.ም ለተከታታይ ሶስት ቀናት በአብርሆት ቤተ- መጻሕፍት የሚካሄድ መሆኑን ምክትል ቢሮ ኃላፊው አስፋው ለገሰ ገልጸዋል።

የመርሃ ግብሩ ዋነኛ አላማ ማህበረሰቡ የንባብ ባህሉን እንዲያዳብርና በከተማው የሚገኙ የህዝብ ቤተ- መጻሕፍት እና መጻህፍት ሻጮች ጠንካራ ትስስር እንዲኖራቸው መሆኑን ተናግረዋል።

በአምስተኛው ከተማ አቀፍ የንባብ ባህል ሳምንት 48 ተቋማት የመጻሕፍት አውደ-ራዕይ እንደሚያቀርቡ ተገልጿል።

በአውደ-ራዕዩ 25 የመንግስት ቤተ መጻህፍት እና 23 የግል መጻሕፍ ሻጮች ይሳተፋሉ ተብሏል።

የአብርሆትቤተ-መጻሕፍት ሀላፊ ኢንጅነር ውብአየሁ ማሞ፤ የተሻለ አስተሳሰብ ያለው ትውልድ ለመፍጠር እና የተሻለች አገር ለመገንባት የማንበብ ባህልን ማጠናከር ይገባል ብለዋል።

ለአብርሆት ቤተ መጽሃፍት “ሚሊዮን መጽሀፍ ለሚሊኒየሙ ትውልድ” በሚል መሪ ሃሳብ እየተካሄደ ባለው የመጽሀፍት ማሰባሰቢያ መርሀ ግብር ከ500 ሺህ በላይ መጻህፍት ማሰባሰብ መቻሉን ጠቁመዋል።

አምስተኛው የንባብ ባህል ሳምንት "በማንበብ የዳበረ አእምሮ ለህብረ ብሔራዊ መግባባት" በሚል መሪ ኃሳብ ይካሄዳል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም