ከ8 ሚሊዮን ኩንታል በላይ የአፈር ማዳበሪያ ለአርሶ አደሩ እየቀረበ ነው

113

ግንቦት 22/2014 (ኢዜአ) ከውጭ አገር ከተገዛው የአፈር ማዳበሪያ ውስጥ ከ8 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ማዳበሪያ አገር ውስጥ ተጓጉዞ ለአርሶ አደሩ እየቀረበ መሆኑን የኢትዮጵያ የግብርና ሥራዎች ኮርፖሬሽን ገለጸ።

የኢትዮጵያ የግብርና ሥራዎች ኮርፖሬሽን ለ2014/15 የሰብል ዘመን 12 ሚሊዮን 876 ሺህ 623 ነጥብ 5 ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ ከውጭ ገዝቻለው ብሏል።

ከዚህ ውስጥ ከጥር እስከ ግንቦት 22/2014 ዓ.ም ድረስ 9 ሚሊዮን 829 ሺህ 190 ኩንታል የአፈር የተለያዩ ማዳበሪያ አይነቶች ጅቡቲ ወደብ መድረሳቸውን ገልጿል።  

ከዚህም 8 ሚሊዮን 243 ሺህ 689 (84 በመቶው) ወደ አገር ውስጥ ተጓጉዞ ለአርሶ አደሩ እየቀረበ መሆኑን የኮርፖሬሽኑ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊው ጋሻው አይችሉህም ተናግረዋል።

ለዘንድሮ የሰብል ዘመን ከሞሮኮው የአፈር ማዳበሪያ አምራች ኩባንያ ኦ ሲ ፒ (OCP) የተገዛው የ ኤን ፒ ኤስ NPS አይነት ማዳበሪያ ወደ ጅቡቲ ወደብ የማጓጓዝ ሥራ ሙሉ በሙሉ ተጠናቋል ብለዋል።

በሌላ በኩል ከውጭ አገር ከተገዛው 5 ሚሊዮን 1 ሺህ 100 ኩንታል ዩሪያ የአፈር ማዳበሪያ ውስጥ በአራት ዙር ጅቡቲ ወደብ የተራገፈው የዩሪያ የአፈር ማዳበሪያ መጠን 1 ሚሊዮን 953 ሺህ 670 ኩንታል (39 በመቶ) ደርሷል ነው ያሉት።

ከሁለት ቀን በኋላ ተጨማሪ 450 ሺህ ኩንታል ዩሪያ ወደብ ይደርሳል ተብሎ እንደሚጠበቅም አብራርተዋል።

ኮርፖሬሽኑ ለዘንድሮ የሰብል ዘመን የገዛው 12 ሚሊዮን የአፈር ማዳበሪያ ኦሲ ፒ እና ፈርቲ ግሎብ ከተሰኙ ዓለም አቀፍ የአፈር ማዳበሪያ አምራች ኩባንያዎች ነው የገዛው።

ለዘንድሮ የሰብል ዘመን ከሞሮኮው ኦ ሲ ፒ ኩባንያ የተገዛው 7 ሚሊዮን 875 ሺህ 523 ነጥብ 4 ኩንታል ኤን ፒ ኤስ (NPS) የአፈር ማዳበሪያ አይነት በ13 መርከቦች ተጓጉዞ ሙሉ በሙሉ ጅቡቲ ወደብ ደርሷል ብለዋል።

በአሁኑ ወቅት ባለፈው ሣምንት የመጨረሻዋ መርከብ ያራገፈችው ኤን ፒ ኤስ (NPS) እና ኤን ፒ ኤስ ቢ ማዳበሪያ ወደ አገር ውስጥ እየተጓጓዘ መሆኑን ከኮርፖሬሽኑ የተገኘው መረጃ ያሳያል።                            

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም