በአሜሪካ የሚገኙ የዳያስፖራ አባላት ኤች አር 6600 እና ኤስ 3199 ረቂቅ ሕጎች እንዳይጸድቁ የተለያዩ እንቅስቃሴዎች እያደረጉ ነው

73

ግንቦት 22 ቀን 2014 (ኢዜአ) በኢትዮጵያ ላይ ጫና ለማሳደር የተዘጋጁት "ኤች አር 6600" እና "ኤስ 3199" የተሰኙ ረቂቅ ሕጎች እንዳይጸድቁ የተለያዩ እንቅስቃሴዎች እያደረጉ መሆኑን በአሜሪካ የሚኖሩ አንድ የዳያስፖራ አባል ተናገሩ።

'ኢትዮጵያ ስታብላይዜሽን ፒስ ኤንድ ዴሞክራሲ አክት’ ወይም ‘ኤች አር 6600’ ለአሜሪካ ኮንግረስ እንዲቀርብ የተዘጋጀ ረቂቅ ሕግ ሲሆን የዚህ ረቂቅ ሕግ ተጓዳኝ ወይም አጋዥ (ኮምፓኒየን ቢል) የሆነው የኢትዮጵያ 'ፒስ ኤንድ ዴሞክራሲ ፕሮሞሽን አክት ኦፍ 2022’ ወይም ‘ኤስ 3199’ ረቂቅ ሕግም  ለአሜሪካ ሴኔት እንዲቀርብ ተዘጋጅቷል።

‘ኤች አር 6600’  የኮንግረሱ የውጭ ግንኙነት ኮሚቴ ተወያይቶበት ለኮንግረሱ መምራቱ የሚታወስ ሲሆን ኤስ 3199' ረቂቅ ሕግ ሴኔቱ እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ2022 ሊመለከታቸው በጊዜ ሰሌዳው ከያዛቸው ረቂቅ ሕጎች አንዱ ሆኖ እንዲካተት ማድረጉ ይታወሳል።

እነዚህም ሕጎች እንዳይጸድቁ የተለያዩ እንቅስቃሴዎችን እያደረጉ መሆኑን በአሜሪካ የካሊፎርኒያ ግዛት ሎስ አንጀለስ ከተማ ነዋሪ የሆኑት ትውልደ-ኢትዮጵያዊው ዳኛቸው ተሾመ ለኢዜአ ተናግረዋል።

በአሜሪካን አገር የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን "ዊ ካን" እና "ኤፓክ" የተሰኙ ተጽዕኖ ፈጣሪ ስብስቦችን በማቋቋም በኢትዮጵያ ያለውን ነባራዊ ሁኔታ ለማስረዳት እየሰሩ መሆኑን አብራርተዋል።

ሕጎቹ በአገርና ሕዝብ ላይ የሚያሳድሩትን ተጽዕኖ በማስረዳት ለኮንግረስና ለሴኔት አባላቶች የማግባባት ሥራ እየተከናወነ መሆኑን ጠቁመዋል።

በቀጣይ ዓመት ሕዳር ወር በሚካሄደው የመካከለኛ ጊዜ ምርጫ ረቂቅ ሕጎች እንዳይጸድቁ በድምጻቸው ጫና ለማሳደር እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

በአሜሪካን የሚገኙ ኢትዮጵያውያን የምርጫ ድምጻቸውን በመጠቀም የባይደን አስተዳደር ሕጎቹን እንዳያጸድቅ ጫና ማሳደር እድል እንዳላቸው ጠቁመዋል።

በተለይም ደግሞ እነዚህ ሕጎች እንዲጸድቁ ፍላጎት ያላቸው የሴኔት አባላት በምክር ቤቱ ከፍተኛ ድምጽ እንዳያገኙ የማድረግ ሥራ መሥራት እንደሚቻል ገልጸዋል።     

በዚህም ኢትዮጵያን የሚጎዱ ሕጎችን እንዳያወጣና የሚደረገውን ያልተገባ ጫና መቀነስ እንደሚቻል ተናግረዋል።

በሌላ በኩል አሸባሪው የሕወሓት ቡድን ህጻናትን ለጦርነት በማሰለፍ ሲፈጽመው የነበረውን ድርጊት ተቃውሞ በማሰማት አንድ የኮንግረንስ አባል ድርጊቱን እንድታወግዝ ማድረግ መቻሉን ጠቁመዋል።

ይህም ኢትዮጵያ ላይ የሚደረጉ ጫናዎችን ለማስቀረት ዳያስፖራው አሁንም ከፍተኛ ተጽዕኖ የመፍጠር አቅም እንዳለው ኩነቱ አመላካች መሆኑን ነው ያነሱት።

"ኤች አር 6600"  እና "ኤስ 3199" የተሰኙ ረቂቅ ህጎች እንዳይጸድቁ መንግሥትም የተለያዩ የዲፕሎማሲ ጥረቶች እያደረገ መሆኑ ይታወቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም