የኦሮሚያ ክልል ከ20 ሺህ በላይ መጻህፍትን ለአብርሆት ቤተ-መጻህፍት ድጋፍ አደረገ

100

ግንቦት 22 ቀን 2014 (ኢዜአ) የኦሮሚያ ክልል ከተለያዩ አካላት ያሰባሰበውን ከ20 ሺህ በላይ መጻሕፍት ለአብርሆት ቤተ-መጻሕፍት አስረከበ።

ክልሉ ድጋፍ ያደረጋቸው መጻሕፍት በታሪክ፣ በባህል፣ በኪነ-ጥበብ ሥራዎችን ጨምሮ በተለያዩ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ ትኩረት ያደረጉና አብዛኛው በኦሮምኛ ቋንቋ የተጻፉ ናቸው ተብሏል።  

በውጭ ቋንቋ የተጻፉ ማኅበራዊና የተፈጥሮ ሳይንስ ማጣቀሻ መጻሕፍት መኖራቸው ተጠቁሟል።

በኦሮሚያ ክልል በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የማኅበራዊ ክላስተር አስተባባሪ አብዱልሃኪም ሙሉ እንደተናገሩት፤ አብርሆት ቤተ-መጻሕፍት በኢትዮጵያ የንባብ ባህል እንዲዳብር ትልቅ አስተዋጽዖ ያደርጋል።    

ይህንንም ከግምት በማስገባት የኦሮሚያ ክልል ከተለያዩ አካላት ያሰባሰበውን ከ20 ሺህ በላይ መጻሕፍት በዛሬው ዕለት ለቤተ-መጻሕፍቱ ድጋፍ ማድረጉን ጠቁመዋል።

በክልል ደረጃም ምክንያታዊ ትውልድ እንዲፈራና የንባብ ባህል እንዲዳብር እየተሰራ መሆኑም ገልጸዋል።

የጠቅላይ ሚኒስትሩ የማኅበራዊ ጉዳዮች አማካሪ ዲያቆን ዳንኤል ክብረት ድጋፉን ሲረከቡ እንደገለጹት፤ ዛሬ የተደረገው ድጋፍ አዲስ ምዕራፍ የሚከፍት ነው።     

"ለቤተ-መጻህፍቱ በብሔር ብሔረሰቦች ቋንቋ የተጻፉ መጽሃፍት እንዲበረከቱ ጥሪ አቅርበን" ነበር ያሉት ዲያቆን ዳንኤል የዛሬው ድጋፍ ለዚህ ጥሪ ምላሽ የሰጠ ነው ብለዋል።   

በኢትዮጵያዊ ቋንቋ የተጻፉ መጻሕፍት ታሪክን ለቀጣዩ ትውልድ ለማሻገር ያላቸው ፋይዳ ከፍ ያለ መሆኑን ጠቁመው ኢትዮጵያዊያን የበለጠ እንዲተዋወቁ እድል የሚሰጥ መሆኑን አብራርተዋል።

ከዚህ ቀደምም የደቡብ ክልል በተለያዩ ቋንቋዎች የተጻፉ መጻህፍት ማስረከቡን አስታውሰው መሰል ድጋፎች ለአብርሆት ቤተ መጻሕፍት ትልቅ ግብዓት ነው ብለዋል።    

ኦሮሚያ ክልል ዛሬ ያደረገው የመጻሕፍት ድጋፍ ከፍተኛውን ቁጥር ያለው መሆኑን ጠቁመው ድጋፉ ለሌሎች ክልሎችም አርአያ የሚሆን ነው ሲሉ ተናግረዋል።   

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ በበኩላቸው የኢትዮጵያ ብልጽግና የሚመጣው አንባቢ ትውልድ ሲፈጠር ነው፤ የአብርሆት ቤተ-መጻሕፍትም ለዚህ ግብ መሳካት ትልቅ አስተዋጽኦ ያደርጋል ብለዋል።     

አገር በቀል እውቀቶችና ማንነቶች እንዲዳብሩ በማድረግ ረገድ የቤተ-መጻሕፍቱ ወደ ሥራ መግባት ያለው ሚና ቁልፍ በመሆኑ የሚደረገው ድጋፍ ሊጠናከር እንደሚገባም አጽንኦት ሰጥተዋል።

"አንባቢ ትውልድ አፍርተን ኢትዮጵያን በእውቀት ብርሃን ልንሞላት ከሆነ አንድ አብርሆት ብቻ በቂ አይደለም" ያሉት ከንቲባ አዳነች በሌሎች አካባቢዎችም ተጨማሪ ቤተ መጻሕፍት ሊከፈቱ ይገባል ብለዋል።

ይህንን መነሻ በማድረግ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በቅርቡ በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ተጨማሪ ቤተ-መጻሕፍት መክፈቱን ለአብነት ጠቅሰዋል።   

በዛሬው እለት ከኦሮሚያ ክልል በተጨማሪ የጉሌሌ ክፍለ ከተማ ምክር ቤት፣ ሰኔ ዘጠኝ ትምህርት ቤት፣ የኢትዮጵያ ጥናትና ምርምር ተቋም እንዲሁም ፖፕሌሽን ሚዲያ ሴንተር መጻሕፍት ለግሰዋል።    

ኢትዮጵያን እናልማ፣እንገንባ፣እንዘጋጅ

‼️

ሀገርን በዘላቂነት እናልማ

‼️

የፈረሰውን አብልጠን እንገንባ

‼️

ለማንኛውም ፈተና እንዘጋጅ

‼️
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም