የኢትዮጵያንና የእስራኤልን የቆየ ወዳጅነት የማጠናከር ፍላጎት እንዳለው አለም አቀፉ የጽዮናውያን ጁዊሽ ኤጀንሲ ገለጸ

177

ጎንደር፤ ግንቦት 22/2014 (ኢዜአ) የኢትዮጵያንና የእስራኤልን የቆየ ወዳጅነትና የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት የማጠናከር ፍላጎት እንዳለው የአለም አቀፉ የጽዮናውያን ጁዊሽ ኤጀንሲ ሊቀ መንበር ሚስተር ያኮቭ ሃጎል ገለጹ።

74 አባላትን የያዘው የእስራኤል የልዑካን ቡድን በጎንደር ከተማ  ጉብኝት እያካሄደ ነው።

የኤጀንሲው ሊቀመንበር ሚስተር ያኮቭ ሃጎል  እንደገለጹት ኢትዮጵያና እስራኤል ካላቸው የረጅም ጊዜ ታሪካዊ ግንኙነት አንጻር ጠንካራ  የሕዝብ ለሕዝብ ትስስር ፈጥረዋል።

በተለይ ግብርና፣ ጤና፣ ትምህርትና የንግድ ዘርፎች ሁለቱ ሀገራት ጠንካራ ኢኮኖሚያዊ ግንኙነት የመሰረቱባቸው  መሆናቸውን ጠቁመዋል።

 በርካታ ኢትዮጵያውያን በእስራኤል ሀገር ኑሯአቸውን መስርተው እንደሚገኙ አመልክተው፤ ይህም የሁለቱን ሀገራት የቆየ ወዳጅነትን ይበልጥ ማጠናከር አስችሏል ብለዋል፡፡

ኤጀንሲው በተለያዩ የአለም ክፍል የሚገኙ እስራኤላውያንን በማገናኘት በኩል የተለያዩ ተግባራትን እያከናወነ መሆኑን ጠቁመው፤ ኢትዮጵያ ውስጥም በርካታ ቤተ-እስራኤላውያን አገልግሎቱን እንዲያገኙ እያገዘ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡

በጎንደርና አካባቢው በርካታ ቤተ-እስራኤላውያን እንደሚገኙ ገልጸው፤ ለጎንደር ከተማ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ አቶ ዘውዱ ማለደ እስራኤልን  እንዲጎበኙ ግብዣ አቅርበውላቸዋል፡፡

የጎንደር ከተማ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ አቶ ዘውዱ ማለደ  በበኩላቸው የጎንደር ከተማ በአለም አቀፍ ቅርስነት የተመዘገቡ የበርካታ ሰው ሰራሽ ቅርሶች ባለቤትና የቱሪዝም መዳረሻ ስፍራ መሆኗን ገልጸዋል።

ጎንደር የሰሜን ተራሮች ብሔራዊ ፓርክና የጣና ሀይቅ ገደማት ማቋረጫ ስትራቴጂያዊ ከተማ መሆኑዋን ጠቁመው በኢንቨስትመንትና በቱሪዝም መስኩ እምቅ የተፈጥሮ ሀብት ያላት መሆኗን  አክለዋል፡፡  

የልዑካን ቡድኑ ታሪካዊና ጥንታዊ ወደ ሆነችው ጎንደር ከተማ መምጣቱ የሁለቱን ሀገራት ግንኙነት ያጠናክራል ብለዋል።

ይህም በኢንቨስትመንትና በቱሪዝም ዘርፍ የእስራኤል ቱሪስቶችና ባለሀብቶችን ለመሳብ አመቺ ሁኔታ እንደሚፈጥር ተናግረዋል።

ጎንደር ከተማ እስራኤል ሀገር ከሚገኙ ከቴላቪቭና ሂፓ ከተሞች ጋር የእህትማማች ከተሞች ግንኙነት እንደመሰረተች ጠቁመው፤ እህት ከተሞቹ  ግንኙነታቸውን ለማጠናከር በሚያስችሉ ጉዳዮች በትብብር እየሰሩ መሆናቸውንም ጠቁመዋል፡፡  

የልዑካን ቡድኑ በቆይታው በጎንደር ከተማ የሚገኙ ታሪካዊ የቱሪዝም መዳረሻዎችን ጨምሮ የቤተ-እስራኤላውያን የእምነት ቦታዎችን እንደሚጎበኙም  ታውቋል፡፡

ለልዑካን ቡድኑ መሪ ከእንጨት ቅርጽ የተሰራ የፋሲል አብያተ መንግሰት ወካይ ምስል በጎንደር ከተማ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ አቶ ዘውዱ ማለደ ስጦታ ተበርክቶላቸዋል።   

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም