የህክምና አገልግሎት አሰጣጥን ለማሻሻል የተጀመሩ ስራዎች ለውጥ እያስመዘገቡ ነው

188

ግንቦት 22/2014 (ኢዜአ) በኢትዮጵያ የህክምና አገልግሎት አሰጣጥን ለማሻሻል የተጀመሩ ስራዎች ከወዲሁ ለውጥ እያስመዘገቡ መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ ተናገሩ፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህን ያሉት በዳግማዊ ምኒሊክ ሪፈራል ሆስፒታል የተገነባው የኩላሊት እጥበት ማዕከል በዛሬው ዕለት በተመረቀበት ወቅት ነው።

ማዕከሉ አሁን ላይ በቀን ለ30 ሰው የኩላሊት እጥበት አገልግሎት መስጠት የሚችል ሲሆን በሙሉ አቅሙ መስራት ሲጀምር በቀን ለ90 ታማሚዎች የኩላሊት እጥበት አገልግሎት የሚሰጥ ይሆናል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ በዚህን ወቅት ባደረጉት ንግግር፤ ኢትዮጵያ ውስጥ ሙያን ያማከለ አገልግሎት ከመስጠት ጋር በተያያዘ ችግር እንደነበር አስታውሰዋል፡፡

ለወጡን ተከትሎ በተቋማት ላይ የተሰሩ የለውጥ ስራዎች ሙያና ሙያተኞችን በማገናኘት ረገድ የተሻለ ሁኔታ መፍጠራቸውን አንስተዋል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር እንደ አዲስ  ሲዋቀር ከተሰጠው ተልእኮ አንዱ የጤና አገልገሎትን ማስፋፋት መሆኑን ገልጸው ተስፋ ሰጪ ጅምሮች መኖራቸውን ገልጸዋል።

ለአገልግሎት የበቃው የኩላሊት እጥበት ማዕከል በዚህ ረገድ የሚጠቀስ ማሳያ መሆኑን ገልጸው ሆስፒታሉ በቀጣይ የአገልግሎት አሰጣጡን ጥራት ይበልጥ እንዲያሳድግ አሳስበዋል፡፡  

በጎ ፈቃደኛ ተማሪዎችንና የህክምና ባለሙያዎችን በመጠቀም የሆስፒታሉን ግቢ ማስዋብ እንደሚገባም እንዲሁ፡፡

በትምህርትና ጤና በመሳሰሉ የማህበራዊ ተቋማት ላይ የአገልግሎት አሰጣጡ ለማስተካከል የተጀመሩ ስራዎች ከወዲሁ ተስፋ ሰጪ ለውጥ እያስመዘገቡ ስለመሆኑም አብራርተዋል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ፤ አዲስ አበባን የጤና ቱሪዝም ማዕከል ለማድረግ ከግሉ ዘርፍ ጋር በመቀናጀት የተለያዩ ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በዛሬው እለት የተመረቀው ማዕከል የዚሁ ስራ አካል መሆኑን ገልጸው በሙሉ አቅሙ ወደ ስራ ሲገባ በቀን ለ30 ሰዎች የኩላሊት እጥበት አገልግሎት እንደሚሰጥ አብራርተዋል፡፡

በቀጣይ ማዕከሉ የኩላሊት ንቅለ ተካላ አገልግሎት መስጠት የሚጀምር መሆኑንም ነው ያነሱት፡፡

በሆስፒታሉ ዘመናዊ የዓይን ህክምና አገልግሎት ለመስጠት የሚያስችሉ ተግባራት በቀጣይ ዓመት እንደሚጀመሩም ጠቁመዋል፡፡  

ከተማ አስተዳደሩ አሁን ላይ  በሆስፒታል ግንባታ ለሚሳተፉ የግል ተቋማት ከሚያደርገው የቦታ አቅርቦት ባሻገር የነባር ሆስፒታሎችን እድሳት እያከናወነ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡

በማዕከሉ ህክምና ሲከታተሉ ካገኘናቸው ህሙማን መካከል ወይዘሮ ፈለቀች አሰፋ፤ የማእከሉ መገንባት   ከተጨማሪ ወጪ ታድጎናል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም