የግብርና ምርታማነትን ለማሳደግ አመራሩ በልዩ ትኩረት መስራት እንዳለበት ተገለጸ

91

ባህር ዳር፤ ግንቦት 22/2014 (ኢዜአ) የአርሶ አደሩን የግብርና ምርትና ምርታማነት ለማሳደግ በየደረጃው ያለው አመራር በልዩ ትኩረት ሊሰራ እንደሚገባ የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ዶክተር ይልቃል ከፋለ አሳሰቡ።

ለ2014/2015 የምርት ዘመን በቅድመ ዝግጅት የተከናወኑ የግብርና ስራዎችን የሚገመግምና በቀጣይ ሥራዎች ላይ የሚመክር መድረክ በባህር ዳር ከተማ እየተካሄደ ነው።

በክልሉ ግብርና ቢሮ በተዘጋጀው መድረክ ላይ ርዕሰ መስተዳድሩን ጨምሮ የክልሉ ከፍተኛ አመራሮች፣ የዞን አስተዳዳሪዎች፣ የፓርቲ ሃላፊዎች፣ የዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንቶች እና በየደረጃው ያሉ የግብርናው ዘርፍ አመራሮች እየተሳተፉ ነው።

ዶክተር ይልቃል በዚህ ወቅት እንደገለጹት ለቀጣይ የመኸር ወቅት አርሶ አደሩ ምርታማነቱን አሳድጎ ውጤታማ እንዲሆን በየደረጃው ያለው አመራር በቅንጅት የክትትልና የድጋፍ ስራዎችን ሊሰራ ይገባል ብለዋል።

የግብርና አመራሩ፣ ባለሙያውና አርሶ አደሩ ተግባብቶና ተቀናጅቶ እንዲሰራ ከፍተኛ አመራሩ በትኩረት መንቀሳቀስ እንዳለበት ጠቁመዋል።

የአርሶ አደሩን ምርትና ምርታማነት በማሳደግ በምግብ እራስን ለመቻል የተያዘው ግብ እንዲሳካ በክልሉ መንግስት በኩል አስፈላጊውን ሁሉ ለማድረግ እንደሚሰራ  አመልክተዋል።

የክልሉ ግብርና ቢሮ ሃላፊ ዶክተር ሃይለማሪያም ከፍያለው በበኩላቸው፣ በ2014/2015 የመኸር ምርት ዘመን 143 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ለማምረት ታቅዶ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

የተያዘው ግብ እንዲሳካም በየደረጃው ያለው አመራርና የግብርና ባለሙያው  ጠንክሮ እንዲሰራ አሳስበዋል።