በጅማ ዞን በዘንድሮው የአረንጓዴ አሻራ መርሀ ግብር 128 ሚሊዮን ችግኞች ለመትከል ዝግጅት እየተደረገ ነው

108

ጅማ ግንቦት 21/ 2014(ኢዜአ) —በጅማ ዞን በዘንድሮው የአረንጓዴ አሻራ መርሀ ግብር 128 ሚሊዮን የዛፍ ችግኞችን ለመትከል የቦታ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን የዞኑ የግብርናና የተፈጥሮ ሀብት ጽህፈት ቤት አስታወቀ፡፡

የጽህፈት ቤቱ ኃላፊ አቶ ኤሊያስ እንድርያስ ለኢዜአ እንደገለጹት በዘንድሮው የአረንጓዴ አሻራ መርሀ ግብር በሁሉም ወረዳዎች የመትከያ ቦታ ዝግጅት እየተደረገ ነው፡፡

እስካሁን ድረስ በዞኑ ባሉ ሁሉም ወረዳዎች ከ35 ሚሊዮን በላይ የመትከያ ጉድጓድ መቆፈሩን ገልጸው የዝግጅት ስራው እንደቀጠለ አስታውቀዋል፡፡

በመሬት መራቆት ምክንያት የሚመጣ የአፈር መሸርሸርን ለመከላከልና የተስተካከለ የአየር ጸባይ እንዲኖር መርሀ ግብሩን አጠናክሮ መቀጠል ተገቢ  ነው ብለዋል።

በክረምቱ መርሀ ግብር የተለያዩ የዛፍ ችግኞችን ለመትከል 70 ሄክታር መሬት መዘጋጀቱን ገልፀው፤  የችግኝ ተከላው ሥራው በህብረተሰቡ ተሳትፎ እንደሚከናወንአስታውቀዋል።

ቀደም ሲል ለተተከሉ ችግኞች ባለሙያዎችና ህብረተሰቡ ልዩ ትኩረት ሰጥተው እንዲንከባከቡ መደረጉን ተናግረዋል፡፡

የዞኑ ነዋሪዎች በበኩላቸው በዘንድሮው የአረንጓዴ አሻራ ልማት የተዘጋጁ የዛፍ ችግኞችን ለመትከል በዘመቻ የመትከያ ጉድጓድ እያዘጋጁ መሆናቸው ገልጸዋል።

በዘንድሮው የአረንጓዴ አሻራ መርሀ ግብር ከዛፍ ችግኝ በተጨማሪ ለምግብነት የሚውሉ የፍራፍሬ ችግኞችን በጓሯቸው ለመትከል ዝግጅት እያደረጉ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡


አምና የተተከሉ ችግኞችን እየተንከባከቡም እንደሆነ አስታውቀዋል፡፡