የፍርድ ቤቶች ጊዜያዊ ዕግድ የመሬት ሃብትን ለምዝበራ፣ሙስና እና ብልሹ አሰራር እየዳረገ መሆኑን አንድ ጥናት አመለከተ

182

ግንቦት 21 ቀን 2014 (ኢዜአ) በአዲስ አበባ የመሬትና መሬት ነክ የፍርድ ቤቶች ጊዜያዊ ዕግድ የመሬት ሃብትን ለምዝበራ፣ ሙስና እና ብልሹ አሰራር እየዳረገ መሆኑን አንድ ጥናት አመለከተ።

የፍትህ አካላት፣ ዳኞች፣ አቃቤያን ሕጎች፣ የፌዴራልና የክልል የስራ ኃላፊዎች በተገኙበት የአዲስ አበባ የመሬትና መሬት ነክ ጉዳዮች እና ጊዜያዊ ዕግዶችን አስመልክቶ በቀረበ ጥናት ላይ ውይይት ተደርጓል።

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሕግ መምህሩ ዶክተር ሙራዱ አብዶ፤ የጥናቱን ግኝት ያቀረቡ ሲሆን የመሬትና መሬት ነክ ሀብቶች ጊዜያዊ ዕግዶች በተቋማት ዘንድ የሚስተዋሉ ችግሮች ለከተማ አስተዳደሩና ህዝቡ ጥቅም ላይ መጠነ ሰፊ አሉታዊ ተጽዕኖ እያደረሰ መሆኑን ገልጸዋል።

በመሬትና መሬት ነክ ጉዳዮች የፍርድ ቤት ጊዜያዊ ዕግድ የመሬት ሃብትን ለምዝበራ፣ሙስና እና ብልሹ አሰራር እየዳረገው መሆኑንም አስረድተዋል።

ለመሰረተ ልማትና ኢንቨስትመንት መጓተትና ወጭ መናር፣ አስተዳደሩን በደራሽ ስራዎች መጥመድ እንዲሁም ነዋሪውን ለእንግልት እየዳረገ መሆኑንም ጠቅሰዋል።

የሁከት ይወገድልኝ እና የዕግድ ጉዳዮች በህግ በሚገባ ተብራርቶ የተቀመጠ ነገር አለመኖሩን ጠቅሰው የፍትሐ ብሔር ሕጉ አሁናዊ የዕድገት ደረጃን ታሳቢ ባደረገ አግባብ መሻሻል አለበት ብለዋል።

May be an image of 4 people and indoor

ከሕግ ክፍተት በተጨማሪ በአስተዳደር ዘርፍ ተቋማት የሚታዩ የአሰራር ውስንነቶችም በችግርነት ተጠቅሰዋል።

በመሆኑም በመሬት ጉዳይ የፍርድ ቤት ጊዜያዊ ዕግድ የሕዝብን ጥቅም መሰረት አድርጎ መፈፀም የሚያስችል የአሰራር ስርአት መዘርጋት እንደሚገባ በጥናቱ ተመልክቷል።

የአዲስ አበባ ፍትህ ቢሮ ኃላፊ ፅዋዬ ሙሉነህ፤ የከተማዋን የልማት መጓተት ከሚፈጥሩ ችግሮች መካከል አንዱ የፍርድ ቤት ጊዜያዊ ዕግድ በመሆኑ ችግሩን በማጤን መፍትሄ ያስፈልጋል ብለዋል።

የከተማ አስተዳደሩ የሚከራከርባቸው መሬት ነክ ጉዳዮች የአስተዳደር አካላትና የፍትህ ተቋማት አሰራር ችግር እና ከዕግድ አሰጣጥ ችግሮች መሰረተ ልማትን እያጓተተ እና ህገ ወጥ የመሬት ወረራን እያባባሰ ነው ሲሉ ተናግረዋል።

የፍርድ ቤት ዕግድ የህዝብን ጥቅም ማዕከል ማድረግ እንዳለበት እና 60 ዓመታት ሳይሻሻል የቆየውን የዕግድ ሕግ የማሻሻል ተግባራት ለባለድርሻ አካላት የቤት ስራ መሆኑን ገልጸዋል።

የተቀላጠፈ፣ፍትሀዊ እና የመንግስት ሀብትን በአግባቡ ለመጠቀምና ችግሮችን ለይቶ መፍትሄ ለማበጀት የፍትህ ተቋማት የሕዝብን ጥቅም ለማስጠበቅ በጋራ ሊሰሩ ይገባል ብለዋል።

በቢሮው በርካታ የማሻሻያ ርምጃዎች እየተወሰዱ ስለመሆኑም ወይዘሮ ፅዋዬ ጠቅሰዋል።

የከተማ አስተዳደሩ ከንቲባ አዳነች አቤቤ፤ በጥናቱ የተለዩ ምክረ ሃሳቦችን በመቀበልና ችግሮችን በመፍታት የጋራ አቋም ይዞ ወደ ስራ መግባት ይገባል ብለዋል።

ለዚህም ሁሉም ባለድርሻ አካላት ሃላፊነታቸውን በአግባቡ ለመወጣት እንዲዘጋጁ አሳስበው አዲስ አበባን ይበልጥ ምቹና ዘመናዊ ለማድረግ የሁላችንም የጋራ ጥረት ሊታከልበት ይገባል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም