የአካባቢያችንን ሰላምና ፀጥታ በመጠበቅ የተጀመረውን ለውጥ አጠናክረን እናስቀጥላለን- የድሬዳዋ የሴቶች ሊግ አመራሮችና አባላት

89

ግንቦት 21 ቀን 2014 (ኢዜአ) የአገሪቱን የብልፅግና ጉዞ ለማሳካት ዘላቂ ሰላምን የሚያረጋግጡ ስራዎችን በመስራት የድርሻቸውን ኃላፊነት በቁርጠኝነት እንደሚወጡ የድሬዳዋ የሴቶች ሊግ አመራሮችና አባላት ገለፁ።

“የሴቶች ተሳትፎና ተጠቃሚነት ለሁለንተናዊ ብልፅግና ” በሚል መርህ በድሬዳዋ የብልፅግና ሴቶች ሊግ ጉባኤ እየተካሄደ ነው።

በጉባኤው ላይ የተሳተፉት የድሬዳዋ ሴቶች ሊግ አመራሮች እና አባላት እንደተናገሩት ፤ ለውጡን ተከትሎ የሴቶች ተሳትፎና ተጠቃሚነት እየጎለበት ይገኛል።

በተለይ በገጠር እና በከተማ በሚገኙ የአስተዳደሩ የስልጣን እርከኖች የሴቶች ቁጥር እየተመጣጠነ መምጣቱ የሴቶችን መሠረታዊ የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች በተገቢው መንገድ እንዲመለሱ ማገዙን ገልፀዋል።

እነዚህን ለውጦች በማጠናከር፣የአካባቢውን ሰላምና ፀጥታ በመጠበቅ የተጀመረውን የብልጽግና ጉዞ ዳር ለማድረስ በቁርጠኝነት እንደሚሰሩ አስታውቀዋል።

እየተካሄደ በሚገኘው ጉባኤ ላይ ከፌደራል ሴቶች ሊግ የመጡ እና የድሬዳዋ አመራሮች መልዕክት ያስተላልፋሉ ተብሎ ይጠበቃል።

በጉባኤው ላይ የድሬዳዋ አስተዳደር ምክር ቤት አፈጉባኤ ወይዘሮ ፈቲያ አደን ጨምሮ የፌደራል የሴቶች ሊግ ተወካይ ወይዘሮ ቡዜና አልከድር ፤የድሬዳዋ የብልፅግና ፓርቲ ፅህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ኢብራሂም ዩሱፍ እና በርካታ አመራሮች ተሳታፊ ሆነዋል።