የአማራ ክልል መንግስት ለአርሶ አደሮች 136 የእርሻ ትራክተሮችን አስረከበ

151

ግንቦት 21 ቀን 2014 (ኢዜአ) የአማራ ክልል መንግስት ለአርሶ አደሮች 136 የእርሻ ትራክተሮችን አስረክቧል።

በክልሉ በቁጥር ደረጃ ለመጀመሪያ ጊዜ በሚባል መልኩ የተዘጋጀው የመካናይዜሽን ርክክብ ስነ-ስርአት የክልሉን ርዕሰ መስተዳደር ዶክተር ይልቃል ከፋለን ጨምሮ የክልሉ ከፍተኛ አመራሮች በተገኙበት በባህር ዳር ከተማ እየተከናወነ ነው።

ርዕሰ መስተዳደሩ ዶክተርይልቃል ከፋለ በዚህ ወቅት እንደገለጹት የክልሉ መንግስት በበርካታ ችግሮች ውስጥ ቢሆንም ግብርናውን ለማዘመንና የአርሶ አደሮችን አቅም ለማሳደግ በትኩረት እየሰራ ነው።

ግብርናውን ለማዘመን የሚሰራው ስራ ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።

የክልሉ ግብርና ቢሮ ሃላፊ ዶክተር ሃይለማሪያም ከፍያለው በበኩላቸው በክልሉ በ2014 እና 2015 ዓ.ም የምርት ዘመን ከ4 ነጥብ 8 ሚሊዮን በላይ ሄክታር መሬት በዘር ለመሸፈን የቅድመ ዝግጅት ስራ እየተከናወነ ነው ሲሉ ገልጸዋል።

ለእርሻ ተስማሚ ከሆነው የክልሉ መሬት ውስጥ 2 ሚሊዮን ሄክታሩ በትራክተር ለመታረስ አመች መሆኑን አስረድተው ነገር ግን እስካሁን ባለው ከ 20 በመቶው ያልበለጠው ነው በትራክተር እየታረሰ ያለው ብለዋል።

እስካሁን ባለውም ከ800 ያልበለጡ የእርሻ ትራክተሮች በክልሉ እንደሚገኙ አመልክተው በዚህ አመት ለዘርፋ ሰፊ ትኩረት ተሰጥቶት 1000 ትራክተሮችን ለአርሶ አደሮች ተደራሽ ለማድረግ እየተሰራ ነው ሲሉ ገልጸዋል።

የዛሬውን ጨምሮ እስካሁን ከ300 በላይ ትራክተሮች ለአርሶ አደሮች እንዲደርሱ ተደርጓል ሲሉም ተናግረዋል።

ትራክተሮቹ በባለሀብቶች፣በዩኒቨርሲቲዎችና በአርሶ አደሮች እንደተገዙ የተገለጸ ሲሆን በርክክብ ስነ-ስርአቱ አርሶ አደሮችና የክልሉ ከፍተኛ አመራሮች ተገኝተዋል።