የህብረተሰቡን የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች በተሻለ ብቃት ለመመለስ የአመራሩን አቅም ማሳደግ ያስፈልጋል

154

ሀዋሳ፣ ግንቦት20/2014 (ኢዜአ) የህብረተሰቡን የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች በተሻለ ብቃት ለመመለስ የአመራሩን ግንዛቤና አቅም ማሳደግ እንደሚያስፈልግ በብልጽግና ፓርቲ የደቡብ ክልል ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ጥላሁን ከበደ ገለጹ።

የብልጽግና ፓርቲ በደቡብ ክልል የሁለተኛ ዙር የከፍተኛ አመራሮች ስልጠና በአርባምንጭ፣ ወላይታ ሶዶ፣ ሆሳዕናና ቡታጅራ ከተሞች መሰጠት ተጀምሯል ።

በአርባምንጭ ማዕከል ስልጠናውን ያስጀመሩት በብልጽግና ፓርቲ የደቡብ ክልል ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ጥላሁን ከበደ እንዳሉት አሁን የሚስተዋሉ ውስብስብ ችግሮችን በጽናት ለመሻገር አመራሩ ግንዛቤውንና አቅሙን ማሳደግ አለበት።

ህብረተሰቡ በተለያዩ መድረኮች ያነሳቸውን የልማትና መልካም አስተዳደር ጥያቄዎች በተሻለ ብቃት ለመመለስ የአመራሩን ግንዛቤና አቅም ማሳደግ ይገባል ብለዋል።

የአቅም ማጎልበቻ ስልጠናው በክልሉ በሁሉም በወረዳዎችና ከተማ አስተዳደሮችና የቀበሌ መዋቅር ድረስ  ላሉ አመራሮችና አባላት እንደምቀጥል አስታውቀዋል።

አመራሩ ከህብረተሰቡ የተሰጡ አደራዎችን መመለስ በሚያስችል ሁኔታ ራሱን ለማዘጋጀት ስልጠናውን በአግባቡ መከታተል እንዳለበት አቶ ጥላሁን አሳስበዋል።

ስልጠናው በአርባምንጭ፣ በወላይታ ሶዶ፣ በሆሳዕና እና ቡታጅራ ማዕከላትም በተመሳሳይ ሁኔታ የተጀመረ ሲሆን፣ 1 ሺህ የሚሆኑ የክልል፣ የዞንና የልዩ ወረዳ አመራሮች በመሳተፍ ላይ ናቸው።

ለአምስት ተከታታይ ቀናት በሚቆየው በዚሁ ስልጠና በተለያዩ ይዘቶች የተዘጋጁ ሰነዶች ቀርበዉ ውይይት እንደሚደርጉና የመስክ ጉብኝትና ልምድ ልውውጥ እንደሚካሄድ ተገልጿል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም