በአፋር ክልል ለአሸባሪው ሕወሓት ቡድን ሊተላለፍ የነበረ ከ3 ሺህ 800 ሊትር በላይ ቤንዚን ተያዘ

110

ሰመራ፣ ግንቦት 20 ቀን 2014 (ኢዜአ) በአፋር ክልል ለአሸባሪው የሕወሓት ቡድን ሊተላላፍ የነበረ ከ3 ሺህ 800 ሊትር በላይ ቤንዚን መያዙን በሰመራ-ሎጊያ ከተማ አስተዳደር የሰመራ ክፍለ ከተማ ፖሊስ  አስታወቀ።

የክፍለ ከተማው ፖሊስ አዛዥ ረዳት ኢንስፔክተር ኢብራሂም መሀመድ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ ከሰመራ ከተማ 10 ኪሎ ሜትር ርቀት ወጣ ብሎ በሚገኝ  ልዩ ስሙ “ኡድሃዩ” በሚባል አካባቢ በቁጥቋጦና ድልድይ ስር የተደበቀ 154 ባለ 25 ሊትር ጄሪካን ቤንዚን ትናንት በሕብረተሰቡ ጥቆማ በቁጥጥር ስር ውሏል።

የተያዘው ቤንዚን ከ150 ሺህ ብር በላይ እንደሚያወጣ ተናግረዋል።

በአካባቢዉ ቤንዚኑን ያዘዋውሩ ነበር ተብለዉ የተጠረጠሩ ሶስት ሰዎች ከአንድ ታርጋና ቦሎ ከሌለው ቶዮታ መኪናና አንድ ክላሽንኮቭ ጋር መያዛቸውን አመልክተዋል።

መነሻውን ከሰመራ-ሎግያ ከተማ አድርጎ በኮንትሮባንድ ንግድ ለሕወሓት የሚተላለፉ እቃዎች መጠን ከጊዜ ወደ ጊዜ እየመጨረ መምጣቱን የገለጹት አዛዡ፤ ባለፉት ስድስት ወራት በፈንቲ ረሱ ዞን በኩል ለሽብር ቡድኑ ሊተላለፍ የነበረ ከ25 ሺህ ሊትር በላይ ቤንዚን መያዙን ተናግረዋል።

ቤንዚን፣ ጨዉ፣ ስኳር፣ ቡና፣ ኦሞና ካሜራ ከእቃዎቹ መካከል ይገኙበታል።

ፖሊስና ሚሊሻ ለሽብር ቡድኑ የኮንትሮባንድ እቃዎች እንዳይተላለፉ ቁጥጥርና ክትትል እያደረጉ እንደሚገኙ ነው ረዳት ኢንስፔክተር ኢብራሂም የገለጹት።

የኮንትሮባንድ እንቅስቃሴው መውጫና መግቢያ ቦታዎችን በመለየት ሕብረተሰቡን ያሳተፈ ስራ እየተከናወነ ይገኛልም ብለዋል።

ኢትዮጵያን እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ