ለሀገረ መንግስት ግንባታ ስኬታማነት የመላ ህዝቡ የስራ ባህል መሻሻል ይገባዋል – ርዕሰ መስተዳድር ደስታ ሌዳሞ

131

ሀዋሳ፣ ግንቦት 20 ቀን 2014 (ኢዜአ) ለሀገረ መንግስት ግንባታ ስኬታማነት የአመራሩ፣ የሰራተኛው እንዲሁም የመላው ህዝብ የስራ ባህል ሊሻሻል እንደሚገባው የሲዳማ ብሄራዊ ክልላዊ መንግሥት ርዕሰ መስተዳድር ደስታ ሌዳሞ አስታወቁ።

“አዲስ ፖለቲካዊ እይታ፤ አዲስ አገራዊ እመርታ” በሚል መሪ ሀሳብ በሀዋሳ ከተማ ለስደስት ቀናት በክልሉ ሲካሄድ የቆየው የብልጽግና ፓርቲ ከፍተኛ እና መካከለኛ አመራሮች የአቅም ግንባታ ስልጠና ዛሬ ተጠቋል።

በስልጠናው ማጠቃለያ ላይ የተገኙት ርዕሰ መስተዳድሩ በተለይ ለኢዜአ እንዳሉት፤ ለውጡን የሚገዳደሩ በአካባባያዊነት የታጠሩና የህዝቡን ማህበራዊ አንድነት የሚያናጉ እንዲሁም ለህዝብ ተጠቃሚነትና ለለውጥ ማነቆና አደናቃፊ የሆኑ ተግባራት መወገድ አለባቸው።

በዚህ ረገድ በስልጠናው ላይ የቆዩ አመራሮች በመጀመሪያ ከማይጠቅም አካሄድና አስተሳሰብ ነፃ ሆነው የፓርቲውን አባላት፣ የመንግሥት ሰራተኛውንና በሂደት ህዝቡን መለወጥ እንደሚጠበቅባቸው አስገንዝበዋል።

ህዝብን ተጠቃሚ ማድረግና ሀገረ መንግሥት ግንባታውን ማፋጠን የሚቻለው በአስተሳሰብ የተለወጠ አመራር ሲኖር ነው ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ፤ በአስተሳሰብ እይታ ለውጥ ላይ ያተኮረ ስልጠና መሰጠቱን ገልጸዋል።

በአጠቃላይ ብልጽግና ፓርቲ ያስቀመጣችው ግቦች እና የፓርቲው የመደመር ጉዞ አቋሞች እንዲሳኩ የበቃና ቁርጠኛ አቋም ያለው አመራር ለመፍጠር ጭምር ስልጠናው አስፈላጊ ሆኖ መገኘቱን ተናግረዋል።

በአገልግሎት አሰጣጥ ያሉ ጉድለቶች እንዲታረሙ ፈጣን፣ ቀልጣፋ እና ሁሉንም በአንድ አይን የሚያስተናግድ አገልግሎት ለማስፈን መግባባት ላይ መድረሱን አስታውቀዋል።

ስራ የለኝም ብሎ እሮሮ ከማሰማት ስራን ሳይንቁ ዝቅ ብሎ በመስራት መለወጥ እንደሚገባ ገልጸው፤ የስራ ባህልን መለወጥ ተገቢነት እንዳለው አመልክተዋል።

በበርካታ የስራ ዘርፎች ከተሰማራው ሰው ውስጥ አብዛኛው ሌት ተቀን የመትጋት ችግር እንዳለበትም ገልጸዋል።

በመሆኑም የስራ ባህልን በአመራር ማእቀፍ ብቻ ሳይሆን በሰራተኛውና በምዕላተ ህዝቡ ጭምር ሊሻሻል እንደሚገባው ነው ርዕሰ መስተዳድሩ ያሳሰቡት።

አምራቹ ኃይል በተጋውና በለፋው ልክ ህይወቱን እየለወጠ እንዲሄድ፣ ህዝባችንም ኑሮ እንዲሻሻል ሌብነት፣ አካባባያዊነት፣ በሶሻል ሚዲያ ስም የማጠልሸት፣ ከስልጣን ሽሚያና ፍላጎት ከመሳሰሉ አደናቃፊ ተግባራት መላቀቅ ይገባል ብለዋል።

አሁን የመጣው የአስተሳሰብ ለውጥ በተግባር እየተደገፈ ስር እንዲሰድና የሚፈለገው ለውጥ እንዲመጣ አቅጣጫ መቀመጡን ርዕሰ መስተዳድሩ አስታውቀዋል።

ለኢዜአ አስተያየታቸውን የሰጡ የስልጠናው ተሳታፊዎች ሀገረ መንግስት ግንባታን ውጤታማ ማድረግ የሚቻለው በእያንዳንዱ ዜጋ ውስጥ የአስተሳሰብ ለውጥ ማምጣት ሲቻል እንደሆነ ተናግረዋል።

ይህንን የማስፈጸም ተልዕኮ የተሰጠው በየደረጃው ያለው አመራር በመሆኑ ብልሹ አሰራሮችን በማስቀረትና በመለወጥ ለህዝቡ ተጠቃሚነት መትጋት እንዳለበት ገልጸዋል።

ኢትዮጵያን እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ