በፌደራል ተቋማት ሥር ባሉ ይዞታዎች እንዲከናወኑ በቀረቡ የፕሮጀክት ዲዛይኖች ላይ አስተያየት ለመሰብሰብ ያለመ ኤግዚቢሽን ተከፈተ

37

ግንቦት 20/2014 (ኢዜአ )በመዲናዋ በፌደራል ተቋማት ሥር ባሉ ይዞታዎች እንዲከናወኑ በቀረቡ የልማት ፕሮጀክት ዲዛይኖች ላይ አስተያየት ለመሰብሰብ ያለመ ኤግዚቢሽን ተከፈተ፡፡
 

የፌደራል የመሬት ባንክና ልማት ኮርፖሬሽን ያዘጋጀው ይህ ኤግዚቢሽን ለአንድ ወር የሚቆይ ይሆናል፡፡

በኤግዚቢሽኑ በዋናነት በመዲናዋ በፌደራል ተቋማት ሥር የሚገኙና ለልማት መዋል ያለባቸው ይዞታዎች ላይ ምን አይነት የልማት ፕሮጀክቶች መከናወን እንዳለባቸው የሚያሳዩ ዲዛይኖች ቀርበዋል፡፡

የመሬት ባንክና ልማት ኮርፖሬሽን ዋና ዳይሬክተር ሌንሳ መኮንን፤ እንዲከናወኑ የታቀዱት የልማት ፕሮጀክቶቹ ዋነኛ ዓላማ በአዲስ አበባ መንገዶች ዳር የሚገኙ ይዞታዎች ማራኪ ገጽታ እንዲላበሱ ከማድረግ ባሻገር ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ጥቅማቸውን ማጎልበት መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በዚህ መሰረት የልማት ፕሮጀክት ዲዛይን ለማዘጋጀት ከጠየቁ 11 ድርጅቶች መካከል ሁለቱ ዲዛይናቸውን አሟልተው በኤግዚቢሽኑ ማቅረብ መቻላቸውን ተናግረዋል፡፡

ዲዛይኖቹን በሚመለከት የቴክኒክ ዳኞች ጥቅል ውጤት ከመሰጠታቸው በፊት የሕዝብ አስተያየት ለመሰብሰብ የዛሬው ኤግዚቢሽን መከፈቱንም ነው ያብራሩት፡፡

ለኤግዚቢሽን የቀረቡ ዲዛይኖች የልማት ፕሮጀክቶች ተናበው ካለመሥራት የሚከሰቱ ችግሮችን በመቅረፍ ረገድ ሚናቸው የጎላ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ኤግዚቢሽኑ የተከፈተው በመዲናዋ መስቀል አደባባይ በሚገኘው ዳያስፖራ ማዕከል ነው፡፡