ወጣቶች ራሳቸውን ከሱሰኝነት በመጠበቅ የተሻለች ኢትዮጵያን ለቀጣዩ ትውልድ ለማስረከብ መሥራት ይጠበቅባቸዋል

37

ግንቦት 20/2014 (ኢዜአ ) ወጣቶች ራሳቸውን ከሱሰኝነት በመጠበቅ ለቀጣዩ ትውልድ የተሻለች ኢትዮጵያን ለማስረከብ መሥራት እንደሚጠበቅባቸው የአዲስ አበባ ከተማ ወጣቶች እና ስፖርት ቢሮ ጥሪ አቀረበ፡፡

ቢሮው  ”ከሱስና ጎጂ መጤ ልማዳዊ ድርጊቶች የነጻ ትውልድ ለሀገር እድገት ያለው ሚና ” በሚል መሪ ሃሳብ  ከሁሉም ክፍለ ከተሞች ለተውጣጡ 250  ወጣቶች የግንዛቤ ሥልጠና ሰጥቷል፡፡

የቢሮው ምክትል ኃላፊ ጥበቡ በቀለ፤ በመዲናዋ ብሎም በአገር አቀፍ ደረጃ አስተማማኝ ሰላም ለማስፈንና ከሱስ የፀዳ ትውልድ መገንባት እንደሚገባ አንስተዋል፡፡

በመሆኑም ወጣቶች ”እኔ ለአገሬ ሚናዬ ምንድን ነው?” በሚል እሳቤ የተሻለች ኢትዮጵያን ለመገንባት መሥራት እንዳለባቸው ነው የተናገሩት፡፡

ለዚህ ደግሞ ወጣቶች ራሳቸውን ከሱስና ጎጂ መጤ ልማዶች መጠበቅ እንዳለባቸው ገልጸዋል፡፡

ወጣቶች በሱሰኝነትና በጎጂ መጤ ልማዳዊ ድርጊቶች እንዲጠመዱ ከሚያደርጋቸው ምክንያቶች አንዱ የግንዛቤ ማነስ መሆኑን የተናገሩት ደግሞ የኢትዮ ከሱስ የነጻ ትውልድ በጎ አድራጎት ድርጅት መሥራች ዶክተር  ጃራ ሰማ ናቸው።

በመሆኑም ብቁና ችግር ፈቺ ትውልድ ለማፍራት በተለይ ወጣቶችን በተገቢው መልኩ ማሰልጠን እንደሚገባ አንስተዋል፡፡

ወጣቶችም ግንዛቤያቸውን ለማስፋት በሚረዱ ጉዳዩች ላይ ማተኮር እንዳለባቸው መክረዋል፡፡

በሥልጠናው የተካፈሉ ወጣቶች በበኩላቸው፤ ራሳቸውን ወደ ተሻለ ሁኔታ ለመለወጥ በኃላፊነት መሥራት እንዳለባቸው ገልጸዋል።

ወጣት  አሸናፊ ብርመቹ፤ ከዚህ ቀደም በተለያዩ ሱሶች ተጠምዶ እንደነበር አስታውሶ፤ በተለያዩ ሥልጠናዎች ያገኘውን እውቀትና ክህሎት በመጠቀም ራሱን ከሱስ ነጻ ስለማድረጉ ይናገራል፡፡

ከዚህ አኳያ ሥልጠናው ወጣቶችን በመለወጥ ረገድ ሚናው የጎላ መሆኑን ጠቅሶ፤ መሰል ሥልጠናዎች ለወጣቶች በስፋት ተደራሽ መሆን እንዳለባቸው ጠቁሟል፡፡

ሌላዋ አስተያየት ሰጪ ወጣት ዘርዋ መለሰ በበኩሏ፤ የነገ አገር ተረካቢ ወጣቶች  ከሱስ ነጻ በመሆን ከራሳቸው አልፎ አገራቸውን የመለወጥ ኃላፊነት እንዳለባቸው ተናግራለች፡፡

ከዚህ አኳያ የሚገጥሟቸውን ፈተናዎች ተጋፍጠው በድል ለማለፍ ቁርጠኛ መሆን አለባቸው ነው ያሉት ወጣቶቹ፡፡