የደንብ ጥሰት ቅድመ-መከላከል ሥራ ላይ የሚሰሩ ባለሙያዎች በመጀመሪያ ዲግሪ ደረጃ እንዲሰለጥኑ እየተደረገ ነው

28

ግንቦት 20/2014 (ኢዜአ ) የደንብ ጥሰት ቅድመ-መከላከል ሥራ ላይ የሚሰሩ ባለሙያዎች በመጀመሪያ ዲግሪ ደረጃ እንዲሰለጥኑ እየተደረገ መሆኑን የአዲስ አበባ ደንብ ማስከበር ባለሥልጣን አስታወቀ።

ባለሥልጣኑ በአዲስ መልኩ ያዘጋጀውን አደረጃጀት በሚመለከት በሥሩ ካሉ የክፍለ ከተማና ወረዳ አመራሮች ጋር  ዛሬ ተወያይቷል።

የባለሥልጣኑ የሥልጠና ክፍል ዳይሬክተር ላቀች ኃይሌ እንዳሉት፤ በመዲናዋ የደንብ መተላለፍ  ተግባራት በቁጥርና በዓይነት እየጨመሩ መጥተዋል።

በአሁኑ ወቅት የደንብ ጥሰት ቅድመ-መከላከል ሥራ ላይ የሚሰሩ ባለሙያዎች በመጀመሪያ ዲግሪ ደረጃ እንዲሰለጥኑ እየተደረገ ነው ብለዋል።

ይህም የሚፈለገውን ለውጥ በማምጣት ረገድ ሚናው የጎላ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የመሬት ወረራ፣ ሕገ-ወጥ ግንባታ፣ የጎዳና ላይ ንግድ፣ ሕገ-ወጥ እርድን ጨምሮ በርካታ የደንብ ጥሰቶች መኖራቸውን ጠቁመው፤ ሕብረተሰቡን ያላሳተፉ የመከላከል ተግባራት ካልተካሄደ ችግሩን ማቃለል እንደማይቻል ነው ያመለከቱት።  

በተቋሙ ብቻ የሚከናወኑ ሥራዎች የሚፈለገውን ለውጥ እንደማያመጡ ገልጸው፤ ከዚህ አኳያ ሕብረተሰቡን በማሳተፍ ሕገ-ወጥነትን ለመከላከል በተቀናጀ መልኩ ለመከላከል እንደሚሰራም ነው ያስታወቁት፡፡

በዚህም ተቋሙ ከኃይማኖት ተቋማት እንዲሁም ከሴቶችና ወጣት አደረጃጀቶች ጋር በቅንጅት እንደሚሰራም አክለዋል።

በአሁኑ ወቅት በደንብ ማስከበር ሥራ ላይ የሚሳተፉ በጎ ፈቃደኞች መኖራቸውን ጠቁመው፤ ይህ በጎ ተግባር ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባ አብራርተዋል።    

የግንዛቤ ማስጨበጫ ተግባራት ላይ በስፋት በመሥራት የደንብ ጥሰትን የሚጸየፍ ማኅበረሰብ ለመፍጠር እንደሚሰራም እንዲሁ።  

የባለሥልጣኑ ዋና ሥራ አስኪያጅ ሻለቃ ዘሪሁን ተፈራ በበኩላቸው፤ ባለሥልጣኑ በመዲናዋ የሚስተዋሉ የደንብ  ጥሰቶችን በሚፈታ መልኩ እየተደራጀ መሆኑን ተናግረዋል።   

ለደንብ ማስከበር ጥሰቶች ተጋላጭ የሆኑ አካባቢዎችን በመለየት ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በቅንጅት እየተሰራ መሆኑንም አንስተዋል።

ከአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ ደንብ ማስከበር ጽህፈት ቤት የመጡት መቶ አለቃ ቦጋለ ዓለሙ፤የደንብ ማስከበር ሥራው ውጤታማ እንዲሆን የሎጂስቲክስ ጥያቄዎች ሊመለሱ ይገባል ብለዋል።    

በተለይም የደንብ ልብስ፣ ጫማና ተሽከርካሪዎች በበቂ ሁኔታ ሊሟሉ እንደሚገባ ነው የገለጹት፡፡