የሀዋሳ ከተማ አስተዳደር በከተማ ልማትና ኮንትራክሽን ዘርፍ በርካታ ስራዎችን አከናውኗል

196

ሀዋሳ፣ ግንቦት 20 ቀን 2014 (ኢዜአ) የሀዋሳ ከተማ አስተዳደር በከተማ ልማትና ኮንትራክሽን ዘርፍ በርካታ የመሰረተ ልማት ስራዎችን እንዳከናወነ የሀዋሳ ከተማ ከንቲባ ረዳት ፕሮፌሰር ፀጋዬ ቱኬ ገለጹ።

በከተማው ምክር ቤት 2ኛ ዙር 7ኛ ዓመት የስራ ዘመን 16ኛ መደበኛ ጉባኤ ላይ የከተማ አስተዳደሩን የዘጠኝ ወራት እቅድ አፈጻጸም ሲያቀርቡ በአስተዳደሩ የተከናወኑ የልማት ተግባራት የላቀ አፈጻጸም የተመዘገበባቸው መሆኑንም ጠቁመዋል።

በአፈጻጸሙ ዙሪያ ከኢዜአ ጋር ቆይታ ያደረጉት ከንቲባው፤ ባለፉት ዘጠኝ ወራት የተከናወኑ የልማት ተግባራት ከእቅድ አንጻር የላቀ አፈጻጸም የተመዘገበባቸው ናቸው ብለዋል።

በተለይም በከተማ ልማትና ኮንትራክሽን ዘርፍ በርካታ የመሰረተ ልማት ስራዎች መከናወናቸውን ገልጸው፤ በተለያዩ ምክንያቶች የተቋረጡና አዳዲስ የመንገድ ፕሮጀክቶች መጠናቀቃቸውን ተናግረዋል።

በከተማው ውስጥ ከ20 ኪሎ ሜትር በላይ የጌጠኛ ድንጋይ ንጣፍ (ኮብል ስቶን) ስራ እየተከናወነ መሆኑን የገለጹት ከንቲባው፤ እግረኛን ከተሽከርካሪ የሚለዩ ዘመናዊ አጥሮች በመንገድ ዳርቻዎች የመትከል ስራ ተሰርቷል ብለዋል።

ከ100 ሚሊየን ብር በላይ ወጪ የተደረገባቸዉና ከ17 ኪሎ ሜትር በላይ የሚሸፍኑ ዘመናዊ የመንገድ ዳር መብራቶች ተጠናቀው አገልግሎት መስጠት መጀመራቸውንም ገልጸዋል።

የአረንጓዴ ልማት ስራውን ማጠናከር፣ ፕላን ማስከበርና ህገወጥ ግንባታን መከላከልም ቀጣይ የትኩረት አቅጣጫዎች ናቸው ብለዋል።

ከተማዋን የቱሪዝም ማዕከል ለማድረግ በርካታ ተግባራት እንደሚከናወኑም ገልጸዋል።

በተቋማት ላይ የሚታየውን የአገልግሎት አሰጣጥ ችግር ለመቅረፍ በጥናት የተደገፈ ስራ እየተከናወነ ነው ብለዋል።

በዚህም የ1 ሺህ 89 ሰዎች የቆዩ ጉዳዮች በ48 መዝገቦች ተደራጅተው ምላሽ እንዲያገኙ የተደረገ ሲሆን አብዛኞቹ የልማት ተነሺዎች መሆናቸውን ጠቅሰዋል።

ፈጣን ምላሽ ለመሰጠት የስራ ሃላፊዎች በሳምንት ሶሶት ቀናት ባለጉዳይ እንዲያስተናግዱ አቅጣጫ መቀመጡን ገልጸዋል።

የኑሮ ውድነት ለመቅረፍ ህብረት ስራ ማህበራትን የማጠናከርና የእሁድ ገበያዎችን የማስፋት ስራ እየተሰራ መሆኑንም አክለዋል።

ህገ ወጥ ንግድ በመፈጸም ህዝቡን የሚያስመርሩ ነጋዴዎች ላይ እርምጃ መውሰድ ላይ በቀጣይ ትኩረት ይደረጋል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም