አስተማማኝ ሰላም ለማስፈን ህግ የማስከበር ጉዳይ ተጠናክሮ መቀጠል አለበት – ምሁራን

51

አዳማ፣ ግንቦት 20/2014/ኢዜአ/ ዜጎች በሀገራቸው ያለምን የፀጥታ ስጋት መኖርና መስራት የሚችሉት አስተማማኝ ሰላም ሲኖር በመሆኑ የህግ የበላይነት የማስከበሩ ጉዳይ ልዩ ትኩረት ሊሰጠውና ተጠናክሮ መቀጠል እንደሚገባው ምሁራን ገለጹ።

ለኢዜአ አስተያየታቸውን የሰጡት ምሁራን እንዳሉት የህብረተሰቡን ደህንነት የመጠበቅ ብሎም ህግና ስርዓትን የማስከበር ሃላፊነት ያለው በህዝብ ይሁንታ የተመረጠው መንግስት ብቻ ነው።

ከምሁራኑ መካከል በኮተቤ ትምህርት ዩኒቨርሲቲ ረዳት ፕሮፌሰር ዋለልኝ እምሩ አንዱ ናቸው።

ረዳት ፕሮፌሰሩ እንደገለፁት ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ልማትን ጨምሮ የዜጎችን ሰላማዊ እንቅስቃሴ የሚጎዱ ግጭቶችና ኢ-መደበኛ አደረጃጀቶችን ለማስወገድ መንግስት የሚጠበቅበትን ሃላፊነት አጠናክሮ መቀጠል አለበት።

“ኢ-መደበኛ አደረጃጀቶች የህግ እውቅና የሌላቸውና በራሳቸው ፍላጎት የሚንቀሳቀሱ ናቸው” ያሉት ረዳት ፕሮፌሰሩ፤ በአሁኑ ጊዜ መንግስት የዜጎችን ሰላምና ደህንነት ለማስጠበቅ በመላ አገሪቱ እየወሰደ ያለው ህግ የማስከበር እርምጃው ውጤታማ ነው የሚል እምነት እንዳላቸው ገልጸዋል።

“ህገ ወጥ እንቅስቃሴዎችን መቆጣጠር በቀዳሚነት ከመንግስት ይጠበቃል” ያሉት ረዳት ፕሮፌሰር ዋለልኝ፤ ማንኛውም አደረጃጀት ህጋዊ መሰረትና እውቅና ሊኖረው እንደሚገባም አስገንዝበዋል።

በተለይ ለሀገር ህልውና አደጋ የሆኑ አደረጃጀቶች በመንግስትና በህዝብ መካከል መተማመን እንዳይኖር ስለሚያደርጉ በተለይም “በዝርፊያ፣ በሽብር፣ የህብረተሰቡን ሰላም በመንሳትና በአፍራሽ ተግባር ላይ የተሰማሩት ተለይተው እርምጃ ሊወሰድባቸው ይገባል” ነው ያሉት።

በተለያየ ዓይነት ህዝብ ውስጥ የገባውን የጦር መሳሪያም በአግባቡ ማስተዳደርና መምራት ካልተቻለ ለሀገር ሰላምና ደህንነት አደጋ በመሆኑ ተመዝግቦ ለምን ዓላማና በማን እጅ መኖር እንደሚገባው መታወቅ እንዳለበት ነው ያሳሰቡት።

ዜጎች በሀገራቸው ያለምንም የፀጥታ ስጋት መኖርና መስራት የሚችሉት አስተማማኝ  ሰላም ሲኖር ነው ያሉት ደግሞ በትምህርት ሚኒስቴር የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ጉዳዮች ዋና ስራ አስፈፃሚ ዶክተር ኤባ ሚጀና ናቸው።

“ሰላም ከሌለ መማር አይቻልም” ያሉት ዶክተር ኤባ፤ ሰላም የሁሉ መሰረት በመሆኑ የህግ ማስከበር ጉዳይ በልዩ ትኩረት ተጠናክሮ መቀጠል እንደሚገባው ነው የተናገሩት።

ህግ የማስከበር ጉዳይ የመንግስት አጀንዳ ብቻ ሳይሆን የህዝብ ጉዳይ ጭምር መሆን አለበት ያሉት ዶክተር ኤባ፤ “ሰላም የለም ማለት የምንፈልገው ልማት፣ እድገትና ኑሮ የለም” ብለዋል።

ዜጎች በሰላም ወጥተው መግባት  የሚችሉት፣ ህፃናት በሰላም ትምህርታቸውን መከታተል የሚችሉት፣ ህግ ሲከበር በመሆኑ ህግ የማስከበር እርምጃው ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ተናግረዋል።

በአንድ አገር ውስጥ “ከጅምሩ ኢ-መደበኛ አደረጃጀት መኖር የለባቸውም” ያሉት ዋና ስራ አስፈፃሚው፤ “የታጠቀ ኢ-መደበኛ አደረጃጀት ከተፈጠረና እንደልቡ ከተንቀሳቀሰ የሀገሪቷ ሰላም ከመታወክ ባለፈ ዜጎች በሰላም ወጥተው መግባትም ሆነ መስራት አይችሉም” ብለዋል።

ማንኛውንም የጦር መሳሪያ መታጠቅ ያለበት አካል በህግ የሚታወቅና ለምን እንደሚያስፈልገው ታምኖበትና ተመዝግቦ ያለ አካል መሆን አለበት ሲሉም ተናግረዋል።

በሁሉም የሀገሪቷ አካባቢዎችና ከተሞች እየተወሰደ ባለው ህግ የማስከበር እርምጃ ላይ ሰላማዊ ዜጎች እንዳይጎዱ ጥንቃቄ መደረግ እንዳለበትም ጨምረው አሳስበዋል።

“እዚያም እዚህም የሚስተዋሉ የፀጥታ ችግሮች ህፃናትን ጨምሮ የዜጎችን የመማር መብት የሚገድብ ነው” ያሉት ደግሞ  በኮተቤ  ትምህርት ዩኒቨርሲቲ የምርምርና ማህበረሰብ አገልግሎት ምክትል ፕሬዝዳንት ዶክተር ጠና በቀለ ናቸው።

በሀገራችን ላይ የተለያየ ፍላጎት ያላቸው የውጭ ሃይሎች ዓላማቸውን ለማስፈፀም በሚያደርጉት እንቅስቃሴ ህፃናትና ሴቶች በስፋት ተጋላጭ እንደሚሆኑም አክለዋል።

በሀገራችን አሁን የሚስተዋለው የሰላም እጦት ችግር “በሌሎች ሀገራት ያየነውን የመፍረስ አደጋ ሊያስከትሉ ስለሚችሉ ዜጎች በህግ መገዛት፤ የህግ የበላይነትም መከበር አለበት” ብለዋል።